ቀጥታ፡

''ኢትዮጵያውን በአንድነት ስንቆምና ስንተባበር የማንሻገረው ፈተና የለም''

ነሐሴ 18/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውን በአንድነት ስንቆምና ስንተባበር የማንሻገረው ፈተና የለም ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።


ምክትል ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በመዲናዋ 6ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግረም " ኢትዮጵያውን በአንድነት ስንቆምና ስንተባበር የማንሻገረው ፈተና የለም" ብለዋል።

በክፍለ ከተማው ስራ የጀመረው የምገባ ማዕከል በቀን አንድ ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንኒያቶች በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም በአንድነት ስንቆምና ስንተባበር የማናልፈው ፈተና የለም ብለዋል።

''እኛ ስንከባበር ሌሎች አገራትም ያከብሩናል፤ የውጭ እርዳታ ለጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ለዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፤ እኛው ተባብረን ከድህነት መውጣት አለብን" ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ምንም ገቢ የሌላቸው ዜጎች እንደማንኛውም ዜጋ ንጹህ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል፤ ለዚህም ደግሞ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከምገባ መርሃግብሩ በተጨማሪ የማዕከሉ ተጠቃሚዎች እራሳቸውን በዘላቂነት አንዲለውጡ የስራ ዕድልና የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚመቻቹላቸውም ተናግረዋል።

የማዕከሉን ግንባታ ያከናወነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ዜጎችን ችግር ለማቃለል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኮርፖሬሽኑ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል።

የማዕከሉን የአንድ ዓመት የምገባ ወጪ ለመሸፈን ቃል የገቡት ባለሃብት አቶ ሙኒር አይረዲን፤ በቀጣይ ምንም ገቢ የሌላቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማገዝ በእቅድ እንደያዙ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አምስት የምገባ ማእከላት ተመርቀው ስራ መጀመራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም