አሸባሪው ህውሃት በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘራውን ከፋፋይ አስተሳሰብና አመለካካት ለመለወጥ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህውሃት በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘራውን ከፋፋይ አስተሳሰብና አመለካካት ለመለወጥ መስራት ይገባል
ነሐሴ 18/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘራውን ከፋፋይ አስተሳሰብና አመለካካት ለመለወጥ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ።
ከ500 በላይ ከመንግስትና የግል ኮሌጆች የተወጣጡ መምህራንን ጨምሮ ከጤና ተቋማት የተወከሉ ሃኪሞችና ነርሶችን ያካተተ ውይይት በየካ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል።
ምሁራኑ በውይይታቸው አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘራውን ከፋፋይ አስተሳሰብና አመለካካት ለመለወጥ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋለ።
ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ መከላከልም እንምዲሁ።
አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ሀገርን ሲዘርፍ መቆየቱን ጠቅሰው ከስልጣን ከወረደ በኋላ ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪው ቡድን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ፋሺዝም የፖለቲካዊ ርዕዮት ዓለም ይከተል እንደነበር የተናገሩት ምሁራኑ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ ጽንፈኛ ብሄርተኝነት ያራምድ እንደነበር ነው ያነሱት።
ቡድኑ በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ተቃራኒ ሐሳቦችን በመግፋት ዜጎችን አፍኖ ኢኮኖሚውን በአንድ ወገን የበላይነት ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ አድርጎ የሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በተሳሳተና በጥላቻ ላይ በተመሰረተ ትርክቱ የትግራይን ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር ለመለያየት ለረጅም ዓመታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
አሁን በሀገሪቱ እያጋጠመ ያለው ችግርም ሕወሃት ኢትዮጵያን ለመበታተን ብዙ ምእራፍ ሲሔድ መቆየቱን የሚያመላክት እንደሆነ ጠቁመዋል።
በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑ ላይ ወታደራዊ ድልን ከማስመዝገብ ባሻገር ለዘመናት የሰራበትን ከፋፋይ አስተሳሰብ እና አመለካካትን ለማስወገድ በልዩ ትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል ምሁራኑ።
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ተክሌ፤ ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን አሁናዊ ችግር ለማለፍ ሁላችንም ያለልዩነት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
በመሆኑም ምሁራን አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን ማሻገር የሚችሉ ሀሳቦች እንዲሰርጹ በመስራት አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በተለይም ደግሞ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር በኢኮኖሚ አሻጥር ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን በማጋለጥ ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከፋፋይ አስተሳሰብና አመለካከቶችን በሚቀይሩ ምሁራዊ ስራዎች ላይም ጭምር በመሳተፍ ሀገርን የማዳን ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክፍለ ከተማው ወቅታዊ ሁኔታውን በመጠቀም የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥሩ አካላትን የሚከታተል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸው በወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ እናደርጋለን ብለዋል።