ቀጥታ፡

የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ የዘር ብዜት ስራዎች በስፋት እንዲከናወኑ ተጠየቀ

ነሐሴ 18/2013 (ኢዜአ)  የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ የዘር ብዜት ስራዎችን በስፋትና በጥራት ማከናወን እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአሰላ ቅርንጫፍ ጎንዴ ኢተያ እርሻ ጣቢያንና የምርጥ ዘር መጋዘንን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉትም የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የሚገጥሙትን ችግሮች እየፈታ የዘር ብዜት ስራውን ይበልጥ ማስፋትና ማሳደግ አለበት ብለዋል።

የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ አባላትና የሚመለከታቸው አካላት የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጁም ጠይቀዋል።

በጉብኝታቸው በማሳ ላይ ያሉ የጤፍ፣ የባቄላ፣ የጎመን፣ የተልባ፣ የሽምብራና የበቆሎ የሰብል ዝርያዎችን እንዲሁም የአሰላ ቅርንጫፍ የምርጥ ዘር መጋዘንና የዘር ማበጠሪያን ተመልክተዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በተመለከቱት የስራ እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልጸው ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር ቦርድ ሰባሳቢ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ለምርጥ ዘር ማባዣ የሚውል ተጨማሪ መሬት ለማግኘት ኮርፖሬሽኑ እየጣረ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአርሶ አደሩን ማሳ ለዘር ማባዣነት ለመጠቀምና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የኮንትራት እርሻ የአሰራር ስምምነት ይተገበራልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም