ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና አደጋ ለመመከትና የመፍትሄ አካል ለመሆን የዲያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና አደጋ ለመመከትና የመፍትሄ አካል ለመሆን የዲያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው
ነሀሴ 18/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና አደጋ ለመመከት በምታደርገው ጥረት ውስጥ የመፍትሄ አካል ለመሆን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ 500 የዲያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው።
የዲያስፖራ አባላት ከጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።
ዲያስፖራዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት አገሪቷ የገጠማትን የውስጥና የውጭ ፈተና በጋራ ለመካፈል፣ ችግሮቹን ለመመከትና የመፍትሄው አካል ለመሆን ነው ተብሏል።
የዲያስፖራ አባላቱ በቆይታቸው ለአገር የሚጠቅሙ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ የኢትዮጵያ የዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ተወካይ አቶ ፍቃዱ አባይ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ የትም፣ መቼም፣ በምንም" የሚለውን ጥሪ በመቀበል፤ ዲያስፖራው ከአገር መከላከያ ጎን መቆሙን ለማሳየት የደም ልገሳ መርሃ ግብር እንደሚያካሂድም ተናግረዋል።
የአሸባሪው ሕወሓት አገር ለማፍረስ የሚያደርገውን እኩይ ተግባርና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመትና ሁለተኛ ዓመት የውሃ ሙሌት የተከናወነበት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግም ዲያስፖራው ግድቡን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም ግድቡን የሚገነቡትን ሠራተኞች በአካል ተገኝተው ያበረታታሉ ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩትን የሸገርና የእንጦጦ እንዲሁም የወዳጅነት ፓርክ እና ሌሎችም የአዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክቶች ይጎበኛሉ።
በተለያዩ ቦታዎች የተጀመሩትን በገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች መካከል ጎርጎራ ፕሮጀከትን ጨምሮ መጎብኘትና ፕሮጀክቶቹን እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊከፈት ያሰበውን የዲያስፖራ ሙዚየም መርዳትና ለተግባራዊነቱ ዲያስፖራውን ማስተባበር ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ዲያስፖራው የአረንጓዴ አሻራ ለማስቀመጥ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደሚያካሄድ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት የማጠቃለያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በዚህም በኢትዮጵያ በሚካሄዱት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የዲያስፖራው ተሳትፎ እንዴት እና በምን መልኩ መጎልበት እንዳለበት ውይይት ይደረጋል ተብሏል።
አዲስ ለሚገነባው ሙዚየም በተለያዩ አገራት የተበተኑትን የኢትዮጵያ ቅርሶች የማስመለስ ሥራም በይፋ እንደሚጀመር ምክር ቤቱ ገልጿል።
በተጓዳኝም የዲያስፖራ አባላቱ አዲስ ለሚመሰረተው መንግሥት የአደራ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ የዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አስተባባሪነት "አባይን እንጎብኝ፣ እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ፣ የፍቅር ጉዞ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው ጉብኝቱ የሚካሄደው።