ለአገር መከላከለያ ሰራዊት ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር መከላከለያ ሰራዊት ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል
ነሃሴ 18/2013 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር ለቆመው የአገር መከላከለያ ሰራዊት ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ሰራተኞች ገለጹ።
ሰራተኞቹ ለአገር መከላከለያ ሰራዊትና በግንባር ለተሰማራው የጸጥታ ሃይል ደማቸውን ለግሰዋል።
ከውጭ ወራሪዎች ጭምር ሉአላዊነቷን አስከብራ የኖረችውን ታላቅ አገር የህወሃት አሸባሪ ቡድን ለማፍረስ መዘጋጀቱ አገር ወዳድ ዜጎችን ሁሉ አስቆጥቷል ብለዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ከፊት ለተሰለፉት የአገር ባለውለታዎች ማንኛውንም ድጋፍና እገዛ እናደርጋለን ነው ያሉት።
በዛሬው እለት አጋርነታቸውን ለመግለጽ ደማቸውን መለገሳቸውን ገልጸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል የክህደት ጥግ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብአዊ ቀውስና እና ቁሳዊ ውድመት እያደረሰ መሆኑንም ሰራተኞቹ ተናግረዋል።
በመሆኑም አሸባሪው ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ የኢትዮጵያ ሰላምና ሉአላዊነት እስከሚረጋገጥ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ተመስገን ጋሮማ፤ ሰራተኞቹ ቀደም ሲል የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለሰራዊቱ መለገሳቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ደግሞ ደማቸውን መለገሳቸውን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ካገኘው ትርፍ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መለገሱንም ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ለሚደረገው ዘመቻ የደርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።