የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ ሀገርን በማዳን ተግባር ውስጥ ከፍተኛ ሚናውን ሊወጣ ይገባል-- የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ ሀገርን በማዳን ተግባር ውስጥ ከፍተኛ ሚናውን ሊወጣ ይገባል-- የፌዴሬሽን ምክር ቤት
አዳማ ነሃሴ 18/2013 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ በህገ መንግስታዊ ስርዓትና ሀገር በማዳን ተግባር ውስጥ የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
በህገ መንግሥት ስርዓት ግንባታ የመገናኛ ብዙሃን ሚናና በ16ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል ።
የፌዴሬሽን ምክርቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ በወቅቱ እንደገለፁት የመገናኛ ብዙሃን በህገ መንግስታዊ ስርዓትና ሀገር በማዳን ተግባር ውስጥ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ።
መገናኛ ብዙሃን ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና በፅናት እንድታልፍ ለህዝቡ ወቅታዊና ተጨባጭ መረጃ በማድረስና የሃሰት ፕሮፖጋንዳን በማክሸፍ ረገድ ሚናቸው የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።
"ተቋማቱ አሁን ላይ ሀገር ለማዳን እያደረጉ ያሉትን ጥረት እናደንቃለን" ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በህልውና ዘመቻው የጀመሩትን ርብርብ አጠናክሮ በማስቀጠል በኩል መገናኛ ብዙሃን ዘርፉ ሚናውን የበለጠ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
"16ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በመጭው አመት በድሬዳዋ ይከበራል" ብለዋል ።
በበዓሉ አሁን የታየው ህዝባዊ መነቃቃት ይበልጥ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ አስተዋጾ እንዳለው ጠቁመው የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ ተገቢውን መረጃ ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።
"ምክር ቤቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ግልጽነትን ለመፍጠርና እንደ ሀገርና ህዝብ ሉዓላዊነታችን ለማስጠበቅ መገናኛ ብዙሃን ላይ በትኩረት መሰራት አለበት" ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው።
"አሁን ያለብንን ችግር ለማለፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉን በበቂ ሁኔታ ማደራጀት ይኖርብናል" ያሉት አምባሳደር ዲና የሀገሪቱን ብዙኋነት ለማስቀጠል ልዩነቶችን ማጥበብና ህብረ ብሔራዊ እንድነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማትና ድርጅቶች ከህወሃት ጋር ባለፍት 44 ዓመታት በፈጠሩት ወዳጅነትና የጥቅም ትስስር አሁን ላይ በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን አመልክተዋል።
"ተቋማቱና ድርጅቶቹ ሀገሪቱ ላይ ዘመቻ እየከፈቱ ያሉት ከለውጡ ወዲህ ጥቅም ስለቀራባቸው እንጂ የዴሞክራሲ መብቶችና ሰብዓዊነት አስጨንቋቸው አይደለም" ሲሉ አምባሳደር ዲና አመልክተዋል።
"አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመገንባት ላይ የሚጠበቅብንን ያህል አልሰራንም" ያሉት አምባሳደር ዲና በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የመገናኛ ብዙኋን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ ኢዲሪስ በበኩላቸው "በሀገራችን ባሉ ከ40 ባለነሱ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በኩል ለህብረተሰቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ማድረስ አለብን" ብለዋል።
"የፌዴራል ስርዓቱን ፈተና ውስጥ የሚያስገባ የሀሰት ፕሮፓጋንዳና ዘመቻ እየተደረገብን ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ ዘመቻዎቹ ግጭት የሚቀሰቅሱና የሚያባብሱ መሆናቸውን አመልክተዋል ።
"መገናኛ ብዙሃኖቻችን ሀገራዊ ሁኔታዎችን በትክክል በመገንዘብ ዘመቻውን ለማክሸፍ በጋራ መስራት ይገባቸዋል" ሲሉ አስገንዝበዋል ።
በመድረኩ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።