የነጋዴዎች ከፍተኛ የትርፍ መጠን /የትርፍ ህዳግ/ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ተጠየቀ

አዲስ አበባ ነሃሴ 18/2013 (ኢዜአ) የነጋዴዎች ከፍተኛ የትርፍ መጠን /የትርፍ ህዳግ/ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ጠየቀ።

በነፃ ገበያ ሥርዓት የገበያው ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን ባለመቻሉ አሁን ላይ ዜጎች በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ይገኛሉ፡፡

በቀናትና በወራት ልዩነት በምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገባቸው መሆኑን በርካቶች የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡

ለሸማቹ ማህብረሰብ መብት መከበር የሚሰራው የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት በሀገሪቱ እየተከሰተ ባለው የዋጋ ግሽበት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ቁምላቸው አበበ፤ "ስግብግብ ነጋዴዎች" በሚፈጥሩት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ዜጎች በኑሮ መወደድ እየተፈተኑ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በርካታ ዜጎች በልተው ለማደር በእጅጉ እየተቸገሩ መሆኑንም አንስተዋል።

በአንዳንድ ተቋማት የመንግስት ሰራተኞች ኑሮአቸውን ለመደጎም ሲሉ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ደንበኞችን ሲያጉላሉ ይታያሉም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት አሁን የመጣ ሳይሆን የቆየ ድምር ውጤት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ቁምላቸው ችግሩን ለማቃለል ለነጋዴዎች የትርፍ ህዳግ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት አንዱ መፍትሄ የትርፍ ህዳግ ማስቀመጥ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ነጋዴዎች እንደፈለጉ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ በመገደብ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ነው የገለጹት።

ከዚህ በተጨማሪ አምራችና ሸማች ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር የሶስተኛ ወገንን ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሃይሉ ዓለሙ፤ ነጋዴው አትርፎ መኖር የሚችለው ሀገር ስትኖር መሆኑን ሊረዳ ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሀገር ለማፍረስ በጋራ እየዶለቱ ባለበት ጊዜ በአቋራጭ ለመክበር የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት።

በዚህም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሌሎችንም የሚያስተምር እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ችግሩን ለመከላከል በሚያደረገው  ጥረት የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶች  ያሉ ሲሆን  በተለይም የትርፍ ህዳግ ገደብ አለመተግበሩ ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የንግድና ገበያ ልማት ሴክተሩ የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና ሎጂስቲክስ ችግር መስተካከል እንዳለበትም እንዲሁ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥሩና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ በቅርቡ መግለጹም የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም