ኅብረተሰቡ በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኅብረተሰቡ በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል
አዲስ አበባ ነሃሴ 18/2013 /ኢዜአ/ኅብረተሰቡ በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ ከመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዳይጋለጥ አፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
በኢትዮጵያ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚጋለጡና በበሽታዎቹ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ የጤና ልማት ጆርናል ከሦስት ዓመታት በፊት ያጠናው ጥናት፤ በተመሳሳይ በአገሪቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሞት ምጣኔ እየጨመረ መጥቷል ብሏል።
በተለይም ደግሞ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ለሞት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥርም ከአጠቃላይ ሞት 42 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑን ነው ጥናቱ ያመላከተው።
ከእነዚህም መካከል 27 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ከ70 ዓመት እድሜ በታች መሆናቸውን በመጠቆም።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የስኳር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል ይላሉ።
በዚህም በርካታ ሰዎች ለስኳር፣ ለደምግፊትና ለተለያዩ ካንሰሮች መጋለጣቸውን ነው የሚናገሩት።
በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል ተጠቃሚነትና ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት መጨመር ለበሽታው አጋላጭ ናቸው ብለዋል።
አሁን ላይ በተለይም ከ30 እስከ 40 የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ላይ በስፋት እየታየ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
በተጨማሪም ኅብረተሰቡ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ሊሆን ስለሚችል አስፈላጊውን የቅድመ ምርመራ ባህል ሊያዳብር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ያም ሆኖ አንዳንድ ታካሚዎች በወቅቱ አስፈላጊውን ሕክምና ባለማድረጋቸው ለሌላ ተጓዳኝ ሕመሞች ጭምር የሚጋለጡበት ሁኔታ ይስተዋላል ነው ያሉት።
በመንግሥት እና በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ከበፊቱ የተሻለ ትኩረት ቢያገኝም አሁንም ሰፊ ሥራ መሰራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ቀድሞ ከመከላከል አኳያ በተለይም ለተማሪዎች በጉዳዩ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተጓዳኝም የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተሉም ምክረ ሃሳብ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ አቶ አዲሱ ወርቁ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሁሉም የእድሜ ክልል ላይ በስፋት እንደሚስተዋል ገልጸዋል።
ስለሆነም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በእድሜ የገፉ ሰዎችን ብቻ ነው የሚያጠቃው የሚለው አመለካከት የተሳሳተ በመሆኑ ሁሉም ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የበሽታው መስፋፋት በማህበረሰቡ የጤና ሁኔታ ላይ እንዲሁም በአገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩም እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
ጎን ለጎንም በጤና ተቋማት የቅድመ ልየታ ሥራዎች መጠናከራቸውን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የግለሰቦችን ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ አጋላጭ ከሆኑ ሁኔታዎች እራስን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል።