ሩሲያ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላት አጋርነት የሚደነቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሩሲያ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላት አጋርነት የሚደነቅ ነው
ነሀሴ 18 /2013 (ኢዜአ) ሩሲያ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላት አጋርነት እና ችግሮቿን ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት መፍታት ትችላለች የሚል ጽኑ እምነቷ የሚደነቅ መሆኑን በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ ገለጹ።
የሩሲያ የዜና አገልግሎት ከአምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።
አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በዚህ ወቅት “ሩሲያ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ያላት መሆኑን አመልክተዋል።
የትግራይ ክልል ክልል ችግር የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት መፍታት ይችላል የሚል አቋም መሳየቷ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የውጭ ሀይሎች መሳተፍ ካለባቸው እንኳ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ሊያግዝ በሚችል መልኩ እንጂ ጣልቃ በመግባት መሆን እንደሌለበት የሩሲያ መንግስት እምነት በመሆኑም ሩስያ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል-አቀባይ ማሪያ ዛኮሮቫ አንዳንድ የምእራባውያን ሚዲያዎችን ችግሮችን ከሚያባብስና ወገንተኛ ከሆነ የመረጃ ስርጭት እንዲቆጠቡና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።