ቀጥታ፡

በጅግጅጋ የተዘርፉ ንብረቶች ለባለቤቶቻቸው እየተመለሱ ነው

ጅግጅጋ ነሀሴ 5/2010 በጅግጅጋ ከተማ ሰሞኑን ተፈጥሮ በነበረው ረብሻ የተዘርፉ ንብረቶች ለባለቤቶቻቸው  የማስመለስ ስራ እየተካሄደ መሆኑን  ፖሊስ ገለጸ፡፡ በጅግጅጋ ከተማ  አስተዳደር የቀበሌ ስድስት ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ሲያድ አህመድ እንዳሉት በረብሻው ወቅት ከተለያዩ የከተማዋ አከባቢዎች የተዘርፉና በየመንገዱ የተጣሉ 22 ባጃጆችና ሁለት የጭነት ተሸከርካሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል እስካሁን 20 ባጃጆችና ሁለት አይሱዝ የጭነት ተሸከርካሪዎች ለባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ለባለሀብቶቹ እንዲመለሱ የተደረጉት የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተራቸውን በማረጋገጥ መሆኑን  አዛዡ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተረጋጋ ሰላም እንዳለ  ያመለከቱት   ምክትል ኢንስፔክተሩ በግጭቱ ወቅት የዜጎች ሀብትና ንብረት የዘረፉ አካላት ለባለቤቶቹ እንዲመልሱ  የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ፖሊስ፣ የቀበሌው አመራር አካላት እና ከህብረተሰብ የተወጣጡ ተወካዮች የጀመሩትን የንብረት ማስመለስ እንቅሰቃሴ ህዝቡ ከጎናቸው በመሆን እንዲያግዝ የጠየቁት ደግሞ የከተማው ቀበሌ ስድስት  ስራ አስኪያጅ አቶ ጉሌድ መሀሙድ ናቸው፡፡ የቀበሌው ነዋሪ የሆነው ወጣት አብዲሰላም ሙባሪክ  በሰጠው አስተያየት በህብረተሰቡና በፖሊስ ጥረት ተዘርፎበት የነበረው የባጃጅ ተሽከርካሪ  ጉዳት ሳይደርስበት  በሰፈር ውስጥ ተገኝተው መረከቡን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ህብረተሰቡን እና የፖሊስ አባላቱን አመስግናዋል፡፡ ወጣት ስንታየሁ ኪዳነ በበኩሉ  በአከባቢያቸው አሁን ያለው ሰላም በዘላቂነት እንዲቀጥል መንግስት የጀመረው ስራ እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡ በአካባቢያቸው በቂ የፀጥታ ኃይል ባለመኖሩ ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ የሰፈር ወጣቶች በፍቃደኝነት እየጠበቁ መሆናቸውን ወጣት ስንታየሁ ተናግሯል፡፡ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት መሐመድ ፈትሒ አብዲ ባለፈው ቅዳሜ በከተማው የተከሰተው ችግር በወቅቱ በቦታው ላይ እንደነበረ አስታውሰው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን በመግለጽ አጥፊዎቹን ኮንኗል፡፡ እንዲህ አይነቱ አደጋ እንዳይደገም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የመቻቻልና የሰላም አስፈላጊት ለማስገንዘብ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም