ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ስምምነት መፈጸሟ የኢኮኖሚ አሻጥር ለመቋቋም ወሳኝ ነው

ዲላ ፤ ነሐሴ 18/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ስምምንት መፈጸሟ የተጋረጠባትን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመቋቋም ወሳኝ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
ዶክተር ዳዊት ሃዬሶ በዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ ሲሆኑ፤ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ መንግስትና ህዝብ እያደረገ ካለው ርብርብ ጎን ለጎን ከአጋዥ ሀገራት ጋር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያደረገችው ስምምነት የአንዳንድ ምዕራባውያንን ጫናን ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም አለው ነው ያሉት።

እንደ ዶክተር ዳዊት  ገለጻ፤ በተለይ እንደ ቱርክና ሩሲያ ያሉ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማይገቡና በጋራ ተጠቃሚነት ከሚያምኑት ጋር ተባብሮ መስራት ጊዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ነው።

በአሸባሪው ህወሀት የስልጣን ዘመን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ቢያሳይም በፈተናዎች የታጀበ እንደነበር ያወሱት ምሁሩ፤ ከእድገቱ በተጣጣመ መልኩ የስራ እድል አለመፍጠርና በየጊዜው እየናረ የሚሄደው የኑሮ ውድነት ለፈተናዎቹ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ህወሀት ኢኮኖሚውን ይመራ የነበረው ሀገርና ህዝብን በማሰብ ሳይሆን የሚቆጣጠራቸውን ድርጅቶችና ጥቂት ግለሰቦች በሚከብሩበት መንገድ እንደነበርም ዶክተር ዳዊት አስታውሰዋል።

ኢኮኖሚውን ለማተራመስ በሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ከቱረክ ጋር የተደረሰው ስምምነት አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ኢኮኖሚውን ለማሽመድመድ የሚያደርጉትን ጫና ለመቋቋም ሀገራችን ሌላ አማራጭ እንዳላት ማሳያ ነው ብለዋል።

የተጋረጠብን ጫና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ከመቋቋም ውጭ አማራጭ የለንም የሚሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአስተደደር ጥናት ኮሌጅ መምህር መሳይ ፍቅሩ ናቸው።

በተለይ በዘመናዊው ዓለም ከግንባር ጦርነት ባልተናነስ መልኩ የኢኮኖሚ ጫና የሚያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከቱርክ ጋር ተባብሮ ለመስራት ስምምነት መፈጸሙ ሁለገብ ጠቀሜታ አለው ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ገበያ መር በሆነ ነጻ ኢኮኖሚ የምትመራ ሃገር ብትሆንም በህወሀት አሻጥር ብሄርን መሰረት ያደረገ ገበያውን ባሻቸው መንገድ የሚዘውሩ ግለሰቦችና የንግድ ተቋማት መፈጠራቸው በአሁኑ ወቅት ዘርፉን  ለማሽመድመድ እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በእነዚህ አካላትም ሆነ ሌሎች ለፖለቲካ አሻጥር ዋጋ በማናር የህዝብን ቁጣ ለመቀስቀስ በሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚወስደው ህጋዊ እርምጃ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተጓዳኝም  የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ መሰራትና ሀገሪቱን ለማዳገም የሚጥሩ አንዳንድ ምዕራባዊያን  በኢኮኖሚው ውስጥ እንዳይገቡ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም