አሸባሪው ህወሓት ሽንፈቱን በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ለማካካስ የሞት ሽረት ጥረት እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ሽንፈቱን በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ለማካካስ የሞት ሽረት ጥረት እያካሄደ ነው

ነሐሴ 17/2013(ኢዜአ) በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘው አሸባሪው ህወሓት በአፋርና በአማራ ክልል በተለያዩ ግንባሮች እየደረሰበት ያለውን ወታደራዊ ሽንፈትንና ኪሳራ ለማካካስ የበሬ ወለደ ውሸቱን በተለይ ለትግራይ ክልል ህዝብና የውጊያ ሞራላቸው ለተጎዳው ታጣቂዎች እያሰራጨ መሆኑን ታማኝ ምንጮች ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
ሰሞኑን አሸባሪው ሰርጎ በገባባቸው የተለያዩ የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ወታደራዊ ኪሰራ የደረሰበት አሸባሪው ህወሓት አመራሮቹን ሰብስቦ ይህን ወታደራዊ ሽንፈትና ውርደት የትግራይ ክልል ህዝብ እንዳያውቀው በምን አይነት መንገድ ትኩረት እናስቀይር በሚል ሃሳብ ሚስጥራዊ ውይይት ማካሄዱም ተገልጿል።
በዚህም በጋይንት ሰባት ክፍለ ጦር እንዲሁም በደሴ ግንባር አንድ ክፍለ ጦር ደምስሰናል በሺዎች የሚቆጠሩ የጠላት ኃይሎችንና መሣሪያዎችን ማርከናል በሚል ሃሰተኛ መረጃ በተለያዩ ልሳኖቹ ለማሠራጨት አቅጣጫ ማስቀመጡን ነው ኢዜአ በክልሉ ከሚገኙ ታማኝ ምንጮች ያረጋገጠው።
አሸባሪው ቡድኑ በጦር አውደውጊያ እየደረሰበት ስላለው ከባድ ሽንፈት የትግራይ ህዝብ እንዲሁም በየግንባሩ ያሰለፋቸው ታጣቂዎች እና ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በግዳጅ መልምሎ በትምህርት ተቋማት የሚያሰለጥናቸው ሰዎች ግንዛቤ እንዳይኖራቸው ፍራቻ ያደረበት መሆኑም ተጠቅሷል።
አሸባሪው አዲስ አበባ ከተማን ለመያዝ ጥቂት እንደቀረው አስመስሎ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እየነዛ መሆኑን የገለጹልን ታማኝ ምንጮቻችን፤ በዚህም በሽንፈትና በአቅርቦት እጥረት ተስፋ የቆረጡትን ታጣቂዎችን አነሳስቶ መልሶ ወደ ግንባር በመላክ ለተጨማሪ እልቂት ለመጋበዝ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሻባሪው ቡድን በተለያዩ ግንባሮች በርካታ አመራሮቹና ታጣቂዎቹ መደምሰሳቸውና መማረካቸው እየታወቀ ፤ አሁንም ልዩ ልዩ የከተማ አካባቢዎችን ስም እየጠቀሰ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በመግለጽ የትግራይ ክልል ህዝብን በማሞኘት ላይ እንደሚገኝም ታማኝ ምንጮች ለኢዜአ ገልጸዋል።
ይህን የመሰለ የበሬ ወለደ ነጭ ውሸት የሚያሰራጨውም በተለያዩ ግንባሮች ሳይዋጋ እጅ የሚሰጥና በሚደርስበት ወታደራዊ ሽንፈት እየተደመሰሰ፤ እየተበታተነና እየፈረጠጠ ባለው ታጣቂ ኃይሉ አማካኝነት በተፈጠረው ከፍተኛ ድንጋጤ ምክንያት የሚይዘውንና የሚጨብጠውን በማጣቱም ተገልጿል።
ይህ በመሆኑም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለመደበቅ የሃሰት ፕሮፖጋንዳን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ለመጠቀም በማቀድ መሆኑ ታውቋል።
በትግራይ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲሁም እንደ ስልክ፣ መብራትና ውሃ ያሉ መሰረተ ልማቶች በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ መቋረጣቸውን የገለጹት ታማኝ ምንጮች፤ በአሸባሪው ቡድን ትምህርት ቤቶች ወደ ጦር ካምፕነት መቀየራቸውን፣ ህጻናትን ለመመልመል የሀገር ሸማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ጭምር ለቅስቀሳ እየተጠቀመ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በተለይ በአፋር ክልል እየተደረገ ባለው አውደ ውጊያ ከፍተኛ ወታደራዊ ሽንፈት የደረሰበት አሸባሪው ቡድን፤ ለሀገሩ አንድነት ከባድ መስዋእትነት በመክፈል ከፍተኛ ወታደራዊ ምት ያሳረፈበትን የአፋር ህዝብ በወታደራዊ አቅም ማሸነፍ ሲያቅተው በጎን ሰርጎ ገቦችን በመላክ ዓላማችን እናንተን ነጻ ለማውጣት ነው የሚል የሀሰት ወሬውን እየነዛ ነው።
በዚህም በመንግስት መዋቅር ለምታገለግሉ ሰዎች በወር ከ8 ሺ ብር በላይ ደመወዝ እንከፍላችኋለን በማለት የቀቢጸ ተስፋ መደለያዎችን በማቅረብ የአልሞት ተጋዳይ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ እንደሆነም ምንጮቻችን ገልጸውልናል።
በአውደ ውጊያው እየደረሰበት ያለውን ወታደራዊ ጫና መቋቋም የተሳነው አሸባሪው ህወሓት ሽንፈቴን በፕሮፖጋንዳ ለማካካስ ያግዘኛል ካለው አሸባሪው የሸኔ ቡድን ጋር በመቀናጀት በህዝብ ዘንድ ምንም ተቀባይነት ያላገኘውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን በሸኔ በኩል ለማናፈስም ሙከራዎችን እያደረገ መሆኑም ነው የተጠቀሰው።
ሰሞኑን አሸባሪው ሸኔ ቡድን የሽብርተኛው ህወሓት ፕሮፖጋንዳን በማስተጋባት ህወሃት እየደረሰበት ያለውን ወታደራዊ ሽንፈት ትኩረት እንዳያገኝ ለማድረግ በአሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎችን መያዙን ፣ትራንስፖርት እናቋርጥባቸኋለን በሚል በማስፈራራትና ኦሮሚያን ነጻ እናወጣለን አኛ ጋር አብራቹህ ቁሙ በማለት ህዝብን ሰላምና መረጋጋት ለመንሳትና በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ለማደናበር ጥረቶችን እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄዱ ባሉት ጦርነቶች ከሀገር መከላከያ፣ ከአማራ ልዩ ሃይል ፣ ከአማራ ሚሊሺያ ፣ ከተለያዩ ክልሎች ልዩ ሃይሎች ከባድ ምት እየደረሰበት የሚገኘው አሸባሪው ህወሓት አላማዬን ያሳካልኛል ብሎ ካሰበው የቅማንት ታጣቂ ቡድን ጋር ትስስር በመፈጠር በመሬት ላይ እየተመዘገበበት ያለውን ሽንፈት ለማካካስ የቅማንት ታጣቂዎችም የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ አድርጓል ነው የተባለው።
የቅማንት ታጣቂ ቅማንት ነጻ መውጣት አለበት፤ ጎንደርን በአጭር ጊዜ ነጻ እናወጣለን የሚሉ የበሬ ወለደ ወሬዎችን ህብረተሰቡ ውስጥ በመንዛት፣ከህዝቡ ገንዘብ ለመሰብሰብና ታጣቂ መልምሎ ለማደራጀት ቢሞክርም ከአማራ ህዝብ ለረጅም አመታት የዘለቅ አብሮነት ያለው የቅማንት ማህበረሰብ እምቢተኝነቱን ከመግለፅ ባለፈ ሰርጎገብ ቅጥረኞች በማጋለጥ ልይ እንደሚገኝም ምንጮቻችን አስታውቀዋል።
ሽብርተኞቹ ህወሓትና ሸኔ እንዲሁም የቅማንት ታጣቂ ቡድን ያልተደረገውን ተደርጓል፣ ያልሆነውን ሆኗል በሚል ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በማሠራጨት መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር በፍጹም የተቃረኑ ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎችን በመልቀቅ ሽንፈታቸውን ለመደበቅ ተከታታይ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ለመረጃው ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡