ቀጥታ፡

የሳዑዲ መንግስት በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረሰ ያለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያቆም ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2013(ኢዜአ) የሳዑዲ መንግስት በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረሰ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያቆም ተጠየቀ።

በሳዑዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሳዑዲ መንግስት እያደረሰ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመቃወም በአዲስ አበባ ሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ተካሂዷል።

"እኔም ለወገኔ ድምፅ ነኝ፣ በሳዑዲ ለሚሰቃዩ ወገኖቼ ዛሬም ነገም ድምጽ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያዊያን ዓለም አቀፍ ወጣቶች ሕብረት ባዘጋጀው በዚህ ሰልፍ የተለያዩ መልእክቶች ተላልፈዋል።

በሰልፉ ላይ "ልጆቻችን በምግብና ውሃ እጥረት በሳዑዲ እስር ቤቶች እየሞቱ ነው፤ እህቶቻችን እየተደፈሩ ነው" በማለት ይህ ኢ- ሰብአዊ ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ተጠይቋል።

ዜጎቹን ለመታደግ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም አሁንም አስቸኳይ እልባት የሚያሻው በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሳዑድን መንግስት እኩይ ተግባር እንዲያወግዝ ተጠይቋል።

የሳዑዲ መንግስት በኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በአስቸኳይ ማቆም አለበትም ብለዋል ሰልፈኞቹ።

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ሕብረት መስራች ቢኒያም ጌታቸው፤ የሳዑዲ መንግስት በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረሰ ያለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሁለቱን አገሮች የቆየ ወዳጅነት የሚጎዳ መሆኑን ገልጿል።

የሳዑዲ መንግስት የሁለቱን አገሮች ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት በእጅጉ የሚያሻክር ተግባር እየፈፀመ በመሆኑ ፍፁም ተቀባይነት የለውም በሚል አውግዘውታል።

በአሁኑ ጊዜ በሳዑዲ እስር ቤቶች ከ3 ሺህ በላይ ነፍሰጡርና ህፃናት በአስከፊ ሁኔታ ይገኛሉ ብሏል የወጣቶች  ህብረት መስራቹ።

በኢትዮጵዊያን በሳዑዲ አረቢያ ሴቶች እየተደፈሩ እንዲሁም በወንዶች ላይ ግዲያ እየተፈፀመ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከቱት ሰልፈኞቹ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ዜጎቹን ከሳዑዲ ማስወጣቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማሳወቅ ሰብዓዊ ቀውሱ ማብቂያ እንዲበጅለት ኢትዮጵያዊያን የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም