ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴና ደብረ ታቦር ከተሞች የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ደሴና ደብረ ታቦር ከተሞች የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
ደሴ፣ ነሃሴ 17/2013 (ኢዜአ ) ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ተፈናቅለው ደሴና ደብረ ታቦር ከተሞች ለተጠለሉ ወገኖችና ለመከላከያ ሰራዊት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ዛሬ በደሴ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት አሸባሪውን ቡድን በጋራ ከመቅበር ባለፈ ተፈናቃዮችን መደገፍና ማቋቋም የግድ ይላል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ካስረከባቸው ድጋፎች መካከል 50 ኩንታል ሩዝ፣ ባለ 3 ሊትር 400 ጀሪካ ዘይት፣ 20 ካርቶን ሳሙና፣ 300 የተለያዩ መመገቢያ ሰሃኖች፣ 400 የውሃ መያዣ ጀሪካኖች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ 200 ጥንድ አንሶላ፣ 500 ብርድ ልብስ፣ 200 የውሃ መያዣጀሪካን፣ 300 የተለያዩ መመገቢያ ስሃኖች፤ 20 ካርቶን ሳሙና ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በኩል ለተፈናቃዮችና ለሰራዊቱ እንዲደርስ መደረጉን ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ ድጋፉም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ሁለንተናዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች የአንድ ወር ደመዛቸውን 22 ሚሊዮን ብር ለመከላከያ ሰራዊት ለመስጠት ቃል መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ በበኩላቸው “በየቀኑ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በጋራ ማለፍ ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
ሁሉም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ በቀረበ ጥሪ መሰረት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ለተፈናቃዮች የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ከማቅረብ ጀምሮ መልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ዩኒቨርሲቲዎች የጀመሩትን አጋርነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“የኢትዮጵዊያንን የአብሮነት፤ የመረዳዳትና የጀግንነት ባህልና እሴትን በመጠበቅ የሀገርን ሉዓላዊነትና ነጻናት በጋራ እናስቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥሪ መሰረት ከዛሬው ድጋፍ ውጭ እስካሁን የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች 6 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።