ቀጥታ፡

ቻይና በኢትዮጵያ ለ150 ሺ መምህራን የሚሆን የኮቪድ 19 ክትባት ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 17/2013(ኢዜአ)ቻይና በኢትዮጵያ ለ150 ሺ መምህራን የሚሆን የኮቪድ 19 ክትባት ድጋፍ አደረገች።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዡአን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ለትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ አስረክበዋል።

ክትባቱ በዋናነት ለትምህርት ዘርፉ የሚውል ሲሆን፤ 150 ሺ መምህራንን ለመከተብ መታሰቡም ተገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መምህራን በስራቸው ባህሪ ምክንያት የበለጠ ተጋላጭ ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ በፊትም ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተለይተው ክትባት ሲሰጥ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

እስካሁንም ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኮቪድ 19 ክትባት መውሰዳቸውን ነው የጠቀሱት።

አሁን የተገኘውን ክትባትም መምህራን ተከታትለው እንዲወስዱ ጥሪ በማቅረብ፤ ከዚህ ጎን ለጎን ቫይረሱን መከላከል ላይ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል።

በዛሬው እለት የቻይና መንግስት ለ150 ሺህ ሰዎች የሚሆን ተጨማሪ 300 ሺህ የኮቪድ 19 ክትባቶችን መለገሷን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት። 

"የቻይና መንግስት ላደረው ድጋፍ ትልቅ ምስጋና ይገባዋል" ያሉት ሚኒስተሯ፤ አሁን ያለው ፍላጎት ብዙ በመሆኑ ድጋፉ እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤ ክትባቱ ለትምህርት ዘርፉ ስኬታማ ጉዞ ትልቅ ጥቅም አለው ነው ያሉት።

ባለፈው ዓመት ብቻ በርካታ መምህራን በኮቪድ 19 ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውንም አስታውሰዋል።

በመላ አገሪቷ ከ700 ሺ በላይ መምህራን በስራ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙት መካከል 50 ሺህ መምህራን ክትባት መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የአሁኑ የቻይና መንግስት ድጋፍም 150 ሺህ መምህራንን ለመከተብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የቻይና መንግስት ምስጋና እንደሚገባው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛኦ ዝዩአን በበኩላቸው የቻይና መንግስት እስካሁን አንድ ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ክትባትም በጤና፣ በመከላከያና በትምህርት ዘርፍ ለተሰማሩ ሰዎች እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የቻይና መንግስት ከመቶ በላይ ለሚሆኑ የዓለም አገራት የኮቪድ 19 ክትባት ድጋፍ እየላከ መሆኑንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል ።

እኤአ 2021 ብቻ ሁለት ቢሊዮን ዶዝ ክትባት ለዓለም ለማድረስ ማቀዷንም ነው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም