ምልምል ሰልጣኞች የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር ለማክሸፍ ስልጠናቸውን በወኔ እየተከታተሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምልምል ሰልጣኞች የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር ለማክሸፍ ስልጠናቸውን በወኔ እየተከታተሉ ነው
ነሐሴ 17/2013(ኢዜአ)በተለያዩ ማሰልጠኛዎች የሚገኙ ምልምል ወታደሮች የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር ለማክሸፍ በእልህና በወኔ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ መሆኑን የአዋሽ አርባ የውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተመስገን አቦሴ ተናገሩ።
በአዋሽ አርባ የውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ለሚሰለጥኑ ምልምል ወታደሮች የአየር ሃይል የኪነ-ጥበብ ቡድን አባላት ዝግጅቶቻቸውን አቅርበዋል።
የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተመስገን አቦሴ በኪነ ጥበብ ዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአገር ህልውና ዘመቻው ሁሉም፣ መቼም፣ በየትም በመዝመት አለኝታነቱን እያሳየ ነው ብለዋል።
አገራዊ ጥሪውን የተቀበሉ ሁሉ በየመስኩ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው የአየር ሃይል የኪነ-ጥበብ ቡድን ዝግጅትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የኪነ-ጥበብ ቡድኑ አባላት የሠራዊቱን ሞራልና ስነ-ልቦና ለማነቃቃት በማሰልጠኛው በመገኘታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።
ምልምል ወታደሮች የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር ለማክሸፍ ስልጠናቸውን በእልህ እየተከታተሉ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።
"ኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ውርሳችን ነው" ያሉት ብርጋዴል ጄኔራሉ የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ የአገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሁላችንም ዝግጁ ነን፤ የኢትዮጵያን ልማትና እድገትም እናስቀጥላለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ተሾመ በዳዳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የለውጥና የልማት ጉዞ በአሸባሪው ህወሓት እኩይ ዓላማ አይደናቀፍም ብለዋል።
ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ የጥፋት ተግባራትን እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም ይህ ዓላማው በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊትና አገር ወዳድ ዜጎች ትብብር እየከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በየትኛውም የጥፋት ሃይል የማትፈርስ ታላቅ አገር መሆኗን በጋራ ከንዳችን እናረጋግጣለን ብለዋል ኮሎኔሉ።