የመዲናዋን ችግሮች ለመቅረፍ የነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ አስተዋፆኦ አለው-ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋን ችግሮች ለመቅረፍ የነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ አስተዋፆኦ አለው-ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2010 ዘርፈ ብዙ የሆነውን የአዲስ አበባ ከተማን ችግር ለመቅረፍ ለሚሰሩት ሥራዎች የመዲናዋ ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንዳለው ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ። ምክትል ከንቲባው የከተማዋን ነዋሪ ችግር ለመቅረፍ መስተዳደሩናና አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አበላት ቅድሚያ ሰጥተው በሚሰሩባቸው መሥኮች ዙሪያ በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህ ጊዜ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እንደገለጹት፤ ዘርፈ ብዙ ለሆነውን የከተማዋ ነዋሪ ችግር መልስ ለመስጠት እንዲቻል የመስተዳደሩን ችግሮች የመለየት፣ አዲስ የካቢኔ አባላትን ማደረጃትና አዳዲስ አደረጃጀትን የመፍጠር ተግባራት ተከናውኗል። በቀጣይም መስተዳደሩ በከተማዋ የሚታየውን የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የቆሻሻ አወጋገድና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል። በንጹህ ውሃ አቅርቦት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የመቅረጽ፣ የውሃ አቅርቦትና የአመራር አደረጃጀት የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ነው። ይህም በከተማዋ የሚታየውን የውሃ መቆራረጥ በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ሲሉ ምክትል ከንቲባው ገለፀዋል። አብዛኛው የከተማዋ የውሃ አቅርቦት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሚገኝ ሲሆን ከክልሉ ጋር በተደራጀ መልኩ እንደሚሰሩም ተናግረዋል። የነዋሪውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከዚህ በፊት የተጀመሩትን ሰፋፊ የቤቶች ግንባታ በአጭር ጊዜ ከማጠናቀቅ በተጓዳኝ በከተማዋ ያሉትን መሬቶች የመለየትና ህዝቡ የቤት ባለቤት እንዲሆን ከግንባታ ጀምሮ የሚሳተፍበት አደረጃጀት ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል። በከተማዋ የሚታየውን የቆሻሻ አወጋገድ ችግር ለመቅረፍ ህዝቡን በማደራጀት ለቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት የተለየ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በከተማ ደረጃ የተደረገውን የአመራር አደረጃጀት በፈጻሚዎችም ዘንድ በመስራት የሥራና የአሰራር መደራረብ ያሉባቸውን ዘርፎች በማስወገድ የተገልጋዩን እንግልት ለማስወገድ በጥናት የተደገፈ ሥራ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል። አዲስ የተደራጀው ኃይል የከተማዋን ችግር የሚያውቅ ከመሆኑም ባሻገር የካቢኔ አባላቱ በብቃታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ የተሾሙ እንደሆነ ተናግረዋል። ስለሆነም የተጀመረውን የሪፎርምና የለውጥ ሥራ ለማስቀጠል የከተማው ነዋሪ ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም እንዲመራና ድጋፍ እንዲያደርግ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ 18 አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት፣ አፈ ጉባኤና ሁለት የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ሹመት ማጽደቁ ይታወሳል።