ቀጥታ፡

ህዝባዊ ማዕበሉ ከአሸባሪ ቡድኖቹ ባለፈ ከጀርባቸው ላሉ የውጪ ኃይሎችም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ነው

ሀዋሳ ኢዜአ ነሀሴ 16/2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለሀገር ህልውና የመቆም ህዝባዊ ማዕበል ተፈረካክሶ እየጠፋ ላለው አሸባሪው ህወሀት ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያን ከጀርባ የሚያሴሩ  የውጭ ኃይሎችም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ነው ይላሉ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፡፡

በሀላባ ዞን የሀላባ ቁሊቶ ከተማና አጎራባች ወረዳዎች ነዋሪዎች ለጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት የሚገልፅና አሸባሪዎቹ ህወሀትና ሸኔን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍና ተካሄደ። 

ከዚህ ጎን ለጎን “እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ” በሚል መሪ ቃል የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አካሂደዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር የሀላባ ዞን ህዝብ ቅድሚያ ለሀገር በመስጠት ድጋፉን ሲገልጽ የቆየ መሆኑን ተናግረዋል።

በህወሀትና መሰሎቹ ሴራ ሀገር ስትነካ ደግሞ ቁጣውን በመግለፅና ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፉን በማድረግ አለኝታነቱን አሳይቷል ብለዋል፡፡

የአሸባሪው ህወሀት ሀገር የማፍረስ ሴራ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በመላው የፀጥታ ኃይልና በህዝቦች የተባበረ ክንድ እየተፈረካከሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ተስፋ በመቁረጥና መድረሻ በማጣት ወደ አጥፍቶ መጥፋት እንቅስቀሴ የገባውን ይህን ኃይል ሰራዊቱ የገባበት በመግባት እየደመሰሰው እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ ያለው የአሸባሪው ህወሀት ሴራ አሁን ያለው የህዝቦች አንድነትና አትንኩን ባይነት እንዳማይሳካ ማሳያ መሆኑን የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የሺዋስ አለሙ ገልጸዋል።

በስፖርቱ ጤናማ ህብረተሰብ የመፍጠርና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ህዝቡን የማንቃት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለሀገሩ ህልውና ዘብ መቆሙን የሚገልፅባቸው መሰል ኩነቶች በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ በበኩላቸው “በህወሀት የክፋት ሴራ ሀገራዊ አንድነታችንን ትተን ልዩነቶቻችን ላይ በማተኮራችን ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት እንዲሁም ለዜጎች በገዛ ሀገራቸው የመሰደድ እጣ ፈንታ ተዳርገን ነበር” ብለዋል።

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት ደጀን ከመሆን ባሻገር ግንባር ድረስ በመዝመት የህወሀትን ሞት ማፋጠን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከዞኑ ግምታቸው ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ 421 ሰንጋዎችና 210 በግና ፍየሎችን ድጋፍ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በጥሬ ገንዘብና በሌሎች ቁሳቁሶች ከተሰበሰበው ድጋፍ ጋር በአጠቃላይ 26 ሚሊዮን 750 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

ከድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ዘቢባ መሀመድ "አሸባሪዎቹ ህወሀትና ሸኔ ሀገራችንን ለማፍረስ ያልተቀደሰ ጋብቻ ቢመሰርቱም እኛ ደግሞ የተቀደሰ አንድነት በመፍጠር ሀገራችንን ማዳን አለብን" ብለዋል።

እስከ አሁን በተለያየ መንገድ ካደረጉት የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ባለፈም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።

“ወንድሞቼ ለሀገር ሲሉ በግንባር እየተዋደቁ ነው” ያለው ወጣት አየነው ሁነኛው በበኩሉ ኢትዮጵያን ለማዳን ከመዝመት ወደ ኋላ እንደማይል ገልጿል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 172 ሰንጋዎችና 88 በግና ፍየሎች ከዞኑ ነዋሪዎች የተሰበሰበ ሲሆን የደም ልገሳም ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም