ደብረ ብርሐን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ 874 ቅድመ መምህራን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ደብረ ብርሐን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ 874 ቅድመ መምህራን አስመረቀ

ነሐሴ 16 /2013 (ኢዜአ) የደብረ ብርሐን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተቀበላችውን 874 ቅድመ መጀመሪያ ትምህርት መምህራን አስመረቀ።
የከተማ አስተዳድሩ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በ2011 ዓ.ም ከደብረ ብርሐን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ጋር 1 ሺህ የቅድመ መጀመሪያ ደረጃ መምህራንን በዲፕሎማ እንዲሰለጥኑ ውል ገብቶ ነበር።
በዚህም ላለፉት ሶስት ዓመታት በቅዳሜና እሁድ ፕሮግራም ቅድመ መጀመሪያ ደረጃ መምህራን ሲሰለጥኑ ቆይተው ተመርቀዋል።
በዛሬው ዕለትም በድምሩ 874 መምህራን በዲፕሎማ ተመርቀዋል።
የኮሌጁ ዲን ታለፍ ፍትህአወቅ፤ አንጋፋው የደብረ ብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ላለፉት 64 ዓመታት በመደበኛ፣ በማታና በርቀት ትምህርት ፕሮግራሞች በርካታ መምህራንን በማሰልጠን ለአገሪቷ ትምህርት መስክ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
ከከተማ አስተዳድሩ ነጻ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው በዕለቱ በኮሌጁ የሰለጠኑ መምህራንም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ገልጸው፤ ለተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎቹ ያገኙትን ዕውቀት ለትውልድ ብርሃን ሆነው ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አደራ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን አገር የማፍረስ እቅድ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ጠቅሰው በጋራ ለመመከት መዘጋጀት አለብን ብለዋል።
የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ የአገሪቷን ህልውና ለማስቀጠል በሚደረገው ትግል ተመራቂዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።