በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው
አዳማ ነሐሴ 15/2013 /ኢዜአ/ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረትና እጥረት ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
የአምራቾች ህብረት ስራ ማህበራትን ከሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር የግብርና ምርት ግብይት ትስስር በመፍጠር የዋጋ ንረትን ለመቀነስ በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በዚህ ጊዜ እንደገለፁት የኑሮ ውድነቱ በከተሞች ሸምቶ በሚኖረው ህብረተሰብ ላይ ሌላ የኢኮኖሚ ጦርነት እየሆነ ይገኛል።
በዩኒየኖች ዘንድ በቂ ምርት መኖሩን የገለፁት አቶ ኡመር ሀገርና ህዝብን የሚደግፍ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ሀገራችን የጀመረችውን የህልውና ዘመቻ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ምግብ ነክ የግብርና ምርቶች ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈፀም በህዝቡ ላይ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ።
“መድረኩ በቂ ምክንያት በሌለው የግብርና ምርቶች የተጋነነ የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረት በህዝቡ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለመቀነስ ያለመ ነው” ብለዋል ።
"አሁን በአሻጥረኞች እየተፈፀመ ያለው የኢኮኖሚ አሻጥር በግንባር ከምንፋለመው ጦርነት ያልተናነሰ በመሆኑ በጋራ ቆመን በመመከት የተረጋጋ የህብረተሰቡን ኑሮ እውን ማድረግ አለብን " ነው ያሉት።
በአምራቹና ሸማቹ መካከል ቀጥታ የገበያ ትስስር በመፍጠር ዋጋ በማረጋጋትና የአቅርቦት ችግር በማቃለል የህብረት ስራ ዩኒየኖችና ማህበረት የበለጠ ሚናቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል ።
"በተለይ አሁን ሀገሪቷ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የሚከሰቱ ምክንያት አልባ የግብርና ምርቶችን የዋጋ ንረት ማቃለል ላይ አሁንም በሙሉ አቅማችን መስራት አለብን" ያሉት ደግሞ የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር ናቸው።
በዚህም የአምራችና የሸማቾች ዩኒዬኖችና ማህበራት የተቀናጀና የተናበበ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል ።
በአሁኑ ወቅት በየቀኑ እየጨመረ ያለውን የግብር ምርቶች የዋጋ ንረት በመከላከል፣ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ይበልጥ መጠናከር አለበት ብለዋል።
በዚህም በዕለቱ 150 ሺህ ኩንታል የግብርና ምርቶች የግዥና ሽያጭ ውልና ከ300ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርት የግዥና ሽያጭ የመግባቢያ ሰነድ ውል ተፈፅሞዋል።
"በዩኒየናችን በቂ ምርትና የማቅረብ አቅም ጭምር አለን" ያሉት ደግሞ የጋለማ ህብረት ስራ ዩኒዬን ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱራማን ገለቶ ናቸው።
ለአርሲ ብቅል ፋብሪካ 40ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ ማቅረባቸውን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ጤፍና ሰንዴ እስከ አዲስ አበባ ድረስ እያቀረቡ መሆኑንም ገልጸዋል።
"በተለይ በግብይትና በምርት አቅርቦት ላይ ለሚፈጠረው ችግር የደላሎች ሰንሰለት ረጅም በመሆኑ መንግስት ቀጥታ አምራቹንና ሸማቹን ማገናኘት ይኖርበታል ነው" ያሉት።
በመድረኩ ላይ ከፌዴራልና ከክልል የተወጣጡ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ዩኒዬኖችና ማህበራት ተሳታፊ ሆኖዋል ።