በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከተላከው ቡና የተገኘው ገቢ አነስተኛ ነው -- ቡናና ሻይ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከተላከው ቡና የተገኘው ገቢ አነስተኛ ነው -- ቡናና ሻይ ባለሥልጣን
ነሀሴ 5/2010 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከተላከው ቡና የተገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የተላከው የቡና ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን ብልጫ ቢያሳይም በገቢ ግን ቀንሷል። ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ 270 ሺህ 388 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ቢሊዮን 157 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ በበጀት አመቱ ለገበያ ከቀረበው 238 ሺህ ቶን በላይ ቡና ከ838 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ለውጭ ገበያ ከተላከ 225 ሺህ ቶን ቡና ከ903 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለፁት አቶ ስንታየሁ ባለፈው በጀት ዓመት የተላከው ቡና በመጠን ብልጫ ቢኖረውም በገቢ ግን ያንሳል። በበጀት ዓመቱ የቡና ምርት ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ እንዲቀርብ 235 ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በቀጥታ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ፣ በየአካባቢው የመጀመሪያ ደረጃ የቡና ግብይት ማዕከላት እንዲቋቋሙ መደረጉንም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። የዓለም የቡና ዋጋ መዋዠቅ፣ ቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የተከሰተ የዝናብ እጥረት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው ያለመረጋጋትና የቡና ምርት ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ ያለመቅረብ ለገቢው መቀነስ ዋና ምክንያት መሆኑንም ነው አቶ ስንታየሁ የተናገሩት። በተያዘው በጀት ዓመት የቡና ምርትንና ገቢን ለማሻሻል አርሶ አደሩ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም፣ደጋፊ የመስኖና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር፣ የምርጥ ዘርና ግብዓቶች አቅርቦትና በየደረጃው የስርጭት ስርኣትን ለመዘርጋት መታቀዱንም የባለስልጣኑ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሳህለማሪያም ገብረመድህን አብራርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከምርምር ማእከላትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል ባለስልጣኑ ይሰራል ያሉት ባለሙያው ህገወጥ የቡና ዝውውርን ለማስቀረት የሚቻልበት አሰራርም ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡ የቡና ላኪው አቶ ሰኢድ አህመዲን በበኩላቸው የዘንድሮ የቡና ምርት በመጠን ከፍ ያለ ቢሆንም በገቢ አነስተኛ የሆነው የአለም የቡና ዋጋ በመዋዠቁ ምክንያት መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡