ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች አሸባሪው ህወሃትን ለመደምሰስ በመዘጋጀት ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች አሸባሪው ህወሃትን ለመደምሰስ በመዘጋጀት ላይ ናቸው
ነሐሴ 15/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማዳን ወደ ማሰለጠኛ የገቡ ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን የአዋሽ አርባ የውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ተመስገን አቦሴ ተናገሩ።
አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ህዝብ በማታለልና በማስገደድ ህጻናትን በመውሰድ "ከነገው ትውልድ ተበድሮ ራሱን ለማኖር የሚመርጥ ኃይል ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
ብርጋዴል ጄኔራል ተመስገን አቦሴ ዛሬ በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ በተለይም ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ለመበተን የሚጥረውን አሸባሪው ህወሃት ለመደምሰስ ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች ዝግጁ ናቸው።
ኢትዮጵያን ለመበተን አሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ከብሔር - ብሔረሰቦች የመጡ ጀግና ወጣቶች በሥልጠና ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሃት ቀድሞውኑ የሚታወቅ ጠላት መሆኑን የገለፁት ብርጋዴል ጄኔራል ተመስገን፤ ቡድኑ "በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በርካታ በደል አድርሶ እና ዝርፊያ ፈፅሞ ከሥልጣን ተገፍቶ የሸሸ ኃይል ነው" ብለዋል።
ቡድኑ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን የመረጠና አንድነት የማይቀበል መሆኑን ያስታወሱት ብርጋዴል ጄኔራል፤ ልዩነትን እንደመኖሪያው አድርጎ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈል ሲሰራ የቆየ አሸባሪ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል።
ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ በማታለልና በማስገደድ ህፃናትን ወደ ጦርነት በመማገድ "ከነገው ትውልድ ተበድሮ ራሱን ለማኖር የሚመርጥ ኃይል ነው" ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ተደምስሶ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሰላምና በልማት እንዲኖር የግድ እንደሚልም ገልፀዋል።
ምልምል ሰልጣኞቹ አሸባሪውን ኃይል ለመደምሰስ ከፍተኛ ሞራል ተላብሰው ሥልጠናቸውን እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
እነዚህን ሰልጣኞች ከዋነው ተዋጊ መከላከያ ኃይል ጋር ተቀላቅለው አሸባሪውን ለመደምሰስ ዝግጁ እንደሆኑ ገልፀዋል።
ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞቹ አገርን ከጠላት የመጠበቅና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በፍላጎታቸው የተነሳሱ መሆኑን አብራርተዋል።