የድሬዳዋ አስተዳደር ባለሃብቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ሰጡ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ አስተዳደር ባለሃብቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ሰጡ

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ባለሃብቶች የሃገርን ህልውና ለመጠበቅ ለሚደረገው ትግል ከ22 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ሰጡ።
በከተማ አስተዳደሩ ''አገራችን ሀብታችን፤ ሀብታችን ለአገራችን'' በሚል መሪ ቃል ባለሀብቶቹ ላደረጉት ድጋፍና ለመከላከያ ሠራዊት ላሳዩት ክብር በተዘጋጀ የምስጋናና የዕውቅና መርሃ-ግብር ላይ እንደተገለጸው ባለሃብቶቹ ከ50 ሺህ እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ድጋፍ አበርክተዋል።
በዚህ ተሳትፏቸው ዕውቅናው የተሰጣቸው ባለሃብቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት ድጋፉን ያደረጉት ሠርቶ ማደግ፤ ልጆች አፍርቶ መኖር የሚቻለው የአገር ሰላም ሲረጋገጥ ነው።
ለሁለተኛ ጊዜ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሰጠው የሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተወካይ አቶ ደጀኔ እስጢፋኖስ እንደተናገሩት ሃብት ማፍራትም ሆነ ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሃገር ሰላም ስትሆን ነው።
''ሠራተኛውም ድርጅቱም የሚኖረው አገር አፍራሹ ቡድን ሲወገድ በመሆኑ የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለን ተልዕኮውን እናሳካለን'' ሲሉም አክለዋል፡፡
''የአገርን ህልውና የማረጋገጡ ተልዕኮ በተባበረ የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ ወንድማማችነትና ድጋፍ ይሳካል'' ያሉት ደግሞ የአዲስ ህይወት ትምህርት ቤት ተወካይ መምህር ዳንኤል የኋላሸት ናቸው፡፡
አፍራሽ ቡድኑ በተባበረ ክንድ ካልተወገደ የመማር ማስተማሩን ሂደትም ዕውን ማድረግ እንደማይቻል የተናገሩት ተወካዩ፤ ከለገሱት 50ሺህ ብር ባለፈ ለሠራዊቱ ልጆች የነጻ ትምህርት(ስኮላርሺፕ)እንሰጣለን ብለዋል፡፡
የኒው ሮድ ግሮሰሪ ተወካይ ወጣት ሄለን አስፋው ''የሚሰራው፣ሀብት የሚገኘው ፣ የምንፈልገውን መሆን የሚቻለው አገር ሰላም ሲሆን በመሆኑ ለአገር ህልውናና ለሰላም መረጋገጥ የምንችለውን ድጋፍ እናደርጋለን'' ብላለች፡፡
የሐረሪ ጫት ላኪዎች ማህበር ተወካይ አቶ አብዲ ኢሌ ዑመር “አገርን ለማዳን የሚካሄደው ዘመቻና ተልዕኮ በድል እስኪጠናቀቅ ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድና የካቢኔ አባላት ለባለሃብቶቹ የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ሰጥተዋል፡፡
ምከትል ከንቲባው ባለሀብቶቹ የጀግናው መከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆን እያደረጉት ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል፡፡
ከአስተዳደሩ የተሰበሰበው ድጋፍ በቅርቡ ወደ ግንባር እንደሚላክም አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደርና ነዋሪዎቹ የአገር አንድነት ለማስከበር ለሚዋደቁት የጸጥታ ሃይሎች የገንዘብና የአይነት አስተዋጽኦ እያደረጉ ሲሆን የአስተዳደሩ ልዩ ሃይልም ወደ ግንባር መዝመቱ ይታወሳል።