አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በምንችለው ሁሉ በመፋለም የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን - የትግራይ ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በምንችለው ሁሉ በመፋለም የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን - የትግራይ ተወላጆች
ነሀሴ 15/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የቀደመ ክብሯና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንድትቀጥል አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በመፋለም ላይ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን እንሆናለን ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።
የሽብር ቡድኑ አገር የማጥፋትና ሕዝቦችን የመለያየት የሴራ እንቅስቃሴ "የአገር ክህደት" ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ተወላጆቹ ቡድኑ ከወራት በፊት የአገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸም ጀምሮ ዛሬም ድረስ አገር ለማፍረስና ለመበተን ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እየነዛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሚያሰራጨው ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳም የትግራይ ወጣቶችና ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ ለተለያዩ ችግሮች እየዳረገ በመሆኑ ለትግራይ ሕዝብ ደህንነት ፈጽሞ ግድ የማይሰጠው እንደሆነ እያሳየ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ አገር ከማፍረስ ተግባሩ በተጨማሪ በሕዝብ ላይ የጥላቻ ትርክት በመንዛት የትግራይን ሕዝብን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲራራቅ እያደረገው ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የጥፋት መሳሪያና መጠቀሚያ እንዳይሆን ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል ብለዋል።
የትግራይ እናቶችና አባቶችን ልጆቻቸውን የጥፋት መሣሪያ በማድረግ እየተጠቀመባቸው ያለውን ወንጀለኛ የሽብር ቡድን እንደሚያወግዙትና እንደሚቃወሙትም ነው የተናገሩት።
ተወላጆቹ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን አገር ለማዳን በሚደረገው ጥረት ለሠራዊቱ ደጀን በመሆንና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በሚፈፅማቸው የጠብ አጫሪነት ትንኮሳዎች ከ300 ሺህ ዜጎች በላይ ከቀያቸው አፈናቅሏል።
በቅርቡም በአፋር ክልል "ጋሊኮማ" በተባለ ሥፍራ ባደረሰው የሽብር ጥቃት 107 ሕጻናትን ጨምሮ የ240 ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል።