ሞዴሊስት ፈቲሃ መሐመድ ለችግረኛ ሕጻናት ከ100ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች አበረከተች - ኢዜአ አማርኛ
ሞዴሊስት ፈቲሃ መሐመድ ለችግረኛ ሕጻናት ከ100ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች አበረከተች
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 15/2013 (ኢዜአ) ዓለም አቀፏ ሞዴሊስት ፈቲሃ መሐመድ በድሬዳዋ ሕፃናት ማቆያ ለሚገኙ ችግረኛ ህጻናት ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች አበረከተች።
ሞዴሊስቷ የአልባሳትና የመጫወቻ ቁሶች ድጋፏን ያደረገችው በድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ለሚገኘው የህፃናት ማቆያ ማዕከል ነው።
ማዕከሉ ከጨቅላ ሕፃናት እስከ ዘጠኝ ዓመት የሞላቸውን ሕጻናትን የሚያቆይበት ሲሆን፤በአሁኑ ወቅት 77 ሕጻናትን እንደሚያሳድግ በድጋፉ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለመሠረት ማኒ ስፖርት አካዳሚ ክለብ ተጫዋቾች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ አበርክታለች፡፡
ሞዴሊስት ፈቲሃ በዚሁ ወቅት ''ከተረዳዳን ፣ ከተረፈን ሳይሆን፤ ካለን ገንዘብና እውቀት ከተባበርን የሀገራችን ችግሮች በራሳችን አቅም መቃለልና መፍታት ይቻላል" ብላለች፡፡
"ጥሩ ነገር ማድረግ አካላዊም መንፈሳዊም ፀጋ ያላብሳል፤ ለህጻናትና ለተቸገሩት ባለን ጥሩ ማድረግና መድገፍ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል'' ስትል መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
በቀጣይም ተመሣሣይ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
ሞዴሊስት ፈቲሃ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት የነገ ሀገር ገንቢና ተረካቢ ሆነው በሥነ ልቡና ጠንክረው እንዲወጡ ያደረገችው ድጋፍ የሚያስመሰግን ነው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ከሪማ ዓሊ ናቸው፡፡
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ በበኩላቸው፤ ፈቲሃ የድሬዳዋን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማሳካት የምታደርገው ድጋፍ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በውጭና ሀገር ውስጥ የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ኮሮና በመከላከል፣ ለችግር የተጋለጡ ህጻናትና ተማሪዎችን በመደገፍ እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናው አቅርበዋል፡፡
ትውልዷ ድሬዳዋ የሆነችው ፈቲሃ በዓለም አቀፍ ሞዴሊስት የምትሰራና የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ውስጥ አባል በመሆንም እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ ኢትዮጵያዊት ናት።
ሞዴሊስቷ የባህልና ቱሪዝም አምባሳደር ተብላ የተሰየመች ሲሆን፤በትውልድ ከተማዋ የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል ጥረት እንደምታደርግ መረጃዎች ያመለክታሉ።