በሐረር ከተማ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች በትራንስፖርት ክፍያ ችግር ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው ለመሄድ መቸገራቸውን ገለጹ

68
አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2010 በትራንስፖርት ክፍያ ችግር ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው ለመሄድ መቸገራቸውን ከኢትዮ ሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በሐረር ከተማ የሚገኙ  ዜጎች ለኢዜአ ገለጹ። የሐረሪ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት አስቸኳይ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ጠቁሟል። በኢትዮ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ሁከት ምክንያት  በርካታ ዜጎች ክልሉን ለቀው በሐረር ከተማ በሚገኘው መንፈሳዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው ይገኛሉ። ኢዜአ በቦታው ተገኝቶ እንደታዘበው የከተማዋ ነዋሪዎች ለተፈናቃዮች በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ በማቅረብና የተለያዩ አልባሳቶችን በመለገስ የወገን አለኝታነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ሆኖም አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተፈናቃዮች እንዳሉት፤ ክልሉን ለቀው ሲወጡ ምንም አይነት ገንዘብ ባለመያዛቸው ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ለትራንስፖርት የሚሆን ክፍያ ለመፈጸም ችግር ገጥሟቸዋል። ቢኒያም አሽኮ ላለፉት ሶስት ዓመታት በጅጅጋ በቀን ስራ ተሰማርቶ ይኖር እንደነበር ገልጾ፤ አሁን በክልሉ ነበረው የፀጥታ ችግር እስኪቀረፍ ወደ ትውልድ አገሩ ሆሳዕና መመለስ እንደሚፈልግ ተናግሯል። ነገር ግን በትራንስፖርት ክፍያ ችግር ምክንያት ወደትውልድ አካባቢው ለመሄድ ተቸግሯል። ወደ ትውልድ ቀዬዋ ሁመራ መመለስ የምትፈልገው አዳነች ታደለም በተመሳሳይ በትራንስፖርት ክፍያ ችግር እየተጉላላች መሆኑን አመልክታለች። የሐረሪ ክልል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይመጅ እድሪስ በበኩላቸው ተፈናቃዮች የመጡበት አግባብ ድንገት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እነርሱን በመቀበልና በማቆየት ረገድ በቅንጅት ሲሰራ እንዳልነበር አክለዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የሚፈልጉ ተፈናቃዮችን የትራንስፖርት ክፍያ በመቻል ሲያጓጉዙ መቆታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ያነሱትን ችግር ለመቅረፍ አስቸኳይ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የተናገሩት ሃላፊው፤ ከነገ ጀምሮ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄድ የሚፈልጉ ተፈናቃዮች ክፍያ ሳይፈጽሙ ትራንስፖርት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ሲቀረፍ መመለስ ለሚፈልጉት ደግሞ በከተማዋ ጊዜያዊ የማቆያ ሸዶች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም