የዓለም ጸኃይ ወዳጆ የጥበብ መድረክ 4ኛው የሽልማት መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ጸኃይ ወዳጆ የጥበብ መድረክ 4ኛው የሽልማት መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ይካሄዳል
ነሀሴ 15/2013 (ኢዜአ) የዓለም ጸኃይ ወዳጆ የጥበብ መድረክ 4ኛው የሽልማት መርኃ ግብር ነሃሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በጸኃፊ ተውኔት፣ አዘጋጅ፣ ገጣሚና የማኅበረሰብ አንቂ ዓለም ጸኃይ ወዳጆ ሥም የተሰየመው የጥበብ መደረኩ በ2011 ዓ.ም ነው በአሜሪካው ኮሎራዶ ግዛት የተመሰረተው።
የጥበብ መድረኩ እስካሁን "ኢትዮጵያ" የተሰኘውን ሽልማት ለጥበብ ንግስቷ ዓለም ጸኃይ ወዳጆች፣ ለድምጻዊ አያሌው መስፍንና ለሳይንቲስት ዶክተር አበራ ሞላ አበርክቷል።
በዘንድሮው የሽልማት መርኃ ግብር ደግሞ አራት አንጋፋና ለአራት ወጣት (ተተኪ) የጥበብ ሰዎች "ኢትዮጵያ" የተሰኘውን የጥበብ መድረኩ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።
በዚህም መሰረት ድምጻዊ አስቴር አወቀ፣ ድምጻዊ አለማየው እሸቴ፣ ገጣሚና የዜማ ባለሙያ ሞገስ ተካ እንዲሁም ገጣሚና ጸሃፊ አያልነህ ሙላቱ ከአንጋፋዎቹ ተሸላሚዎች ናቸው።
ከወጣት ጥበበኞች መካከል ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ፣ ተወናይና ድምጻዊ ሣያት ደምሴ፣ ሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ እንዲሁም ገጣሚና ከያኒ ተስፋሁን ከበደ ሽልማቱ ይሰጣቸዋል ተብሏል።
የጥበብ ሰዎቹ በየሙያቸው ለዘርፉ እድገት ላበረከቱት አስተዋጽዖ እውቅናና ሽልማቱ እንደሚሰጣቸው የጥበብ መድረኩ የቦርድ አማካሪ ጋዜጠኛ ማኅደር በቀለ ገልጿል።
ያም ብቻ ሳይሀን የኢትዮጵያ ባህልና ትውፊት እንዳይረሳና ላበረከቱትም አስተዋጽዖ የሚገባቸውን እውቅና ለመስጠት በማለም የሚካሄድ መርሃ ግብር ነው ብሏል።
እነዚህም ታዋቂ የጥበብ ሰዎች የጥበብ መድረኩ ያቀረባቸውን ተገቢውን መስፈርቶች አሟልተው በመገኘታቸው ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ጋዜጠኛ ማህደር ተናግሯል።
በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በሚካሄደው የሽልማትና የእውቅና መርኃ ግብሩ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም ጸሃይ ወዳጆ የጥበብ መድረክ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች፣ ወጣቶች ከባህላቸውና ከእሴቶቻቸው በኪነ-ጥበብ አማካኝነት እንዲተዋወቁ ይሰራል።
በተጓዳኝም የአገሪቷን ሥነ-ግጥም፣ ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ቴያትርና መሰል የኪነ-ጥበብ ውጤቶች እንዲያድጉ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ የጥበብ መድረክ ነው።