ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልልን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ያለውን የማዕድን ልማትና የግብይት ሂደቱን በማዘመን ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዘርፉ በሚጠናከርበት ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ አሁን ላይ ከግብርናው ቀጥሎ ኢኮኖሚውን እየደገፈ ያለው የማዕድኑ ዘርፍ ነው።

ለዘርፍ ማነቆ የሆኑ የአሰራርና የህግ ማቀፎችን ጭምር በማሻሻል ረገድ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ በተለይም የወርቅ ማዕድን  ልማትና የግብይት ሂደቱን በማዘመን ሀብቱን ለክልሉ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል አመራሩ ለዘርፍ መጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛው የወርቅ ማዕድን በብር በመቀየር ለማስቀመጥ በሚንቀሳቀሱ የኢኮኖሚ ሻጥረኞች ምክንያት አብዛኛው የወርቅ ምርት ወደ ባንክ እየገባ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ፈቃድ በተሰጣቸው የወርቅ አዘዋዋሪዎች አስፈላጊውን ክትትልና ጥናት በማካሄድ እርምጃ መውስድ እንሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ያለውን የወርቅ ሀብት የአመራረትና ግብይት ሰንሰለት ለማዘመን ሚኒስቴሩ  አስፈለጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ኢንጂነር ታከለ አስታውቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ፤ በክልሉ ሰፊ የወርቅ ሀብት ቢኖረም በተፈለው መጠን ለምቶ ለክልሉ ብሎም ለሀገር ጥቅም አለማዋሉን ተናግረዋል።

ሀብቱን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማልማት ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በተለይም የፌደራሉ መንግስት የቴክኖሎጂና የሙያዊ ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ በግብይት ሂደቱም ሆነ በሌሎች የመንግስት መደበኛ ስራዎች እንቅፋት መፈጠሩን አመልክተዋል።

በክልሉ በሚገኙ የዞንና ወረዳ ከተሞች ባንኮች ተደራሽ የሚሆኑበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ በበኩላቸው፤ በክልሉ መንግስት የቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸው፤ የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ የባንክ ቅርንጫፎችን ለመክፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ1 ሺህ 213 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ የተደረገ ሲሆን   በተያዘው የስራ ዘመን ደግሞ 1 ሺህ 600 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማስገባት መታቀዱን በውይይት መድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም