የአሸባሪው ህወሃትን ወረራ ለመቀልበስ ወጣቱ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ እያደረገ ያለው ተጋድሎ ተጠናክሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ህወሃትን ወረራ ለመቀልበስ ወጣቱ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ እያደረገ ያለው ተጋድሎ ተጠናክሯል
ባህር ዳር ነሐሴ 15/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈፀመውን ወረራ ለመቀልበስ ወጣቱ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ በመመከት እያደረገ ያለው ተጋድሎ መጠናከሩን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ አስታወቁ።
ኮሚሽነሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፤ በህልውና ዘመቻው የክልሉ የልዩ ኃይል፣ፖሊስ፣ ሚሊሺያና ፋኖ ከመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየተንቀሳቀሱ ነው።
በተለይ ወጣቱ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆኖ ጠላትን በመመከት እያደረጉ ባለው ተጋድሎ ጠላትን እያዳከመ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የጠላትን መውጫና መግቢያ ከማሳጣት ባለፈ አንገት ለአንገት በመተናነቅ ጭምር ጀብዱ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ንፁሃን ሰዎችን እንደሚገድል፣ ሕዝቡ ያፈራውን ሃብትና ንብረት እንደሚዘርፍ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት የሚገኘው ቡድን በገባበት ሁሉ እንዳይወጣ በፅናት በመፋለም ግብዓተ መሬቱን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ህዝቡ ከፀጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በመሆን ተስፋ የቆረጠውን አሸባሪ ቡድን በገባበት ገብቶ ለመደምሰስ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነር ተኮላ ጥሪ አቅርበዋል።