ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ ከሚረዱ አገራት ጋር ወዳጅነትን ማጠናከር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 15/2013( ኢዜአ) ኢትዮጵያን ያጋጠማት የሕልውና አደጋ ለማለፍ ነባራዊ ሁኔታዋን ከሚረዱ አገራት ጋር ወዳጅነትን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ እንደሚሉት ይህ አካሄድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት ፍላጎት ለሌላቸውና ጎን ለጎንም ጫና ለማሳደር ለሚጥሩ አገራት ምላሽ የሚሰጥ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ተፈሪ መኮንን፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት የነጻነት ታሪክ ያላት አገር ናት ይላሉ።

ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደ አሁኑ ያለ የህልውና ፈተና ሲያጋጥማት አብዛኛውን ጊዜ ምዕራባዊያን አገራት ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ሲያራምዱ እንደነበረ ነው የሚያስታውሱት።

ለአብነትም ከአድዋ ጦርነት በፊት እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዊያን አገራት ኢትዮጵያን በማንኳሰስ ኢጣሊያን ደግሞ ሲደግፉና ማበረታታቸውን አንስተዋል። 

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሲወርድ አብዛኛው የምዕራቡን ክፍል ጨምሮ በወቅቱ የነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር /ሊግ ኦፍ ኔሽን/ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያሳድር አቋም አንጸባርቋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ይህንን ከባድ ፈተናና ጫና በመቋቋም ድል በማድረግ አልገዛም ባይነቷንና ጀግንነቷን ለዓለም በማሳየት እስከ ዛሬ ምሳሌ መሆን ችላለች ነው ያሉት።

ይህ ዘመናትን የተሻገረው አኩሪ የነጻነት ታሪክ በምዕራባዊያን ድጋፍ ሳይሆን በራስ አቅም የመጣና ከ'አልበገር ባይነት ስሜት' የመነጨ መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል።

አሁንም ልክ እንደ ጥንቱ ዜጎች እጅ ለእጅ በመያያዝ አንድነታቸውንና የውስጥ ሠላማቸውን በመጠበቅ የአባቶችን አኩሪ ድል መድገም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እውነታውን ለዓለም አገራት በማጋለጥና ሁኔታውን በማስረዳት ረገድ እየተሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ።

በተለይም እውነታውን በመረዳት ኢትዮጵያን ከሚደግፉ አገራት ጋር ትብብር መፍጠር መጀመርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር መቻል የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ይህ አይነቱ የዲፕሎማሲ አካሄድ ከሌሎች አገራትም ጋር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በተለይ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቱርክ መንግሥት ጋር ያደረጉት ሥምምነት ወቅታዊና አስፈላጊ በመሆኑ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሠላምና የባህል ተመራማሪ ዶክተር ወሰን ባዩ በበኩላቸው የአገራት ግንኙነት በቋሚነት በወዳጅና በጠላት ተፈርጆ የሚጸና አይደለም ይላሉ።

የአገራት ግንኙነት የአገርን ጥቅምና ፍላጎት መሰረት አድርጎ የሚፈጠር መሆኑን ጠቅሰው አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የተለያዩ ሥልቶችን እንደሚቀይሱ ተናግረዋል።

በተለይም ኃያላን አገራት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን በጥቅማጥቅም በመደለል ብሔራዊ ጥቅማቸውን እንዲያሟሉላቸው በደካማ ጎናቸው ሲመጡ ይስተዋላል ብለዋል።

እነዚህ ኃያላን አገራት አፍሪካዊያን ሲያድጉና ሲለወጡ ማየት ስለማይፈልጉ እድገታቸው እንዲሰናከልና የውስጥ ሠላማቸው እንዲናጋ ተግተው ይሰራሉ ነው ያሉት።

አሁንም ኢትዮጵያ ልማቷንና እድገቷን እያረጋገጠች ባለችበት ወቅት ይህን ለማስተጓጎል የሚሰሩ አገራት እንዳሉ ይታወቃል ብለዋል ዶክተር ወሰን።

ስለዚህም አገራቱ ስለ ኢትዮጵያ እውነታውን ከመስማትና ከመረዳት ይልቅ አሸባሪው ቡድን እንደተጎዳ በማስመሰል ሲለሳለሱ ማየት ሰነባብቷል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የተረዱ አገራት ትብብር በኢትዮጵያ ላይ በምዕራባዊያኑ ለሚደርሰው ጫና ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባለፉት ሦስት ዓመታት በድብቅ እንዲሁም ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ እየፈፀመው ያለውን ግልጽ ሽብር እንዲያወግዝ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም