ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያደረገችው ስምምነት ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ያደርሰዋል -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያደረገችው ስምምነት ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ያደርሰዋል -ምሁራን
ሚዛን ፤ ነሐሴ 15/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያደረገችው ስምምነቶች ግንኙነታቸውን ወደላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቱርክ ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያና ቱርክ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመሰራት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ ምሁር አቶ ታደሠ አበራ እንደገለጹት፤ ከቱርክ ጋር የተደረገው የሁለትዮሽ ስምምነት ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማዳከም እየፈጠሩ ያለውን ጫና ለማርገብ ያስችላል።
ከኢትዮጵያ ጋር የ125 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላት ቱርክ አጋዥ በሚያስፈልገን በዚህ አስጨናቂ ወቅት አብራን መቆሟ በተቃራኒው ላሉት የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለ ነው የተናገሩት።
የሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ወቅቱ የሚጠይቀውን የህዝብና ቴክኖሎጂ ዕድገት መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት ካላቸው ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት መጠናከር አለበት ያሉት ምሁሩ ፤ይህም በጸጥታው ዘርፍ ብሎም በሰው ኃይል ልማትና ደህንነት ዙሪያ ጉልህ ሚና መጫወት ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል።
ሌላው የህግ ምሁር አዳነ ኮርቦ በበኩላቸው፤ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
"ቱርክ ከኃያላን ሀገራት መደብ መሆኗ ሌሎች ሀገራት ስለኢትዮጵያ እውነታውን እንዲያጤኑና ዕውነታውን እንዲያውቁ በር ይከፍታል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የህልውና ዘመቻ ተገቢነትና የህወሀትን እኩይ ተግባር ለማጋለጥ ዕድሎችን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
በጅምላ ሲጨፈጭፍና ህጻናትን በጦርነት ያሰለፈውን የአሸባሪው ህወሀት ድርጊት እንዳላየ አልፈው የነጻነት ተሟጋች ነን የሚሉትን ምዕራባውያን ጫና ለመቋቋም እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
እንዲሁም የአሸባሪውን ቡድን ትክክለኛ ማንነት አለም እንዲያውቀው ስምምነቱ ከወቅቱ አንጻር ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የዲፕሎማሲ ስራዋን በተለያዩ መንገዶች ማስፋት ይጠበቅባታል።