ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሓት ከፋፋይ ባህሪይ በቀድሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አንደበት

አቶ መሀመድ ሀሰን ለረጅም ዓመታት በቤልጅየም ነዋሪ የሆኑ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ናቸው። እ.እ.አ በ1990ዎቹ በዋሽንግተን እንዲሁም በብራሰልስ የኢትዮጰያ ዲፕሎማት በመሆን አገልግለዋል። በ1970ዎቹ ደግሞ የኢትዮጰያ ተማሪዎች ንቅናቄ አባል ነበሩ። አቶ መሀመድ ሀሰን በሀገሪቱ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከ Break through  ፕሮግራም አዘጋጅ ራኒያ ካሌክ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ መሀመድ ሁሴን በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለው ችግር መንስኤው በአብዛኛው የሚያያዘው የውጭ ሃይሎች ከሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ጋር አያይዘው ይገልጻሉ። የውጭ ሃይሎች በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ መንግስት እንዳይፈጠር በዘርና በጎሳ እንዲከፋፈሉ የተለያዩ ስልቶችን እንደሚጠቀሙ ያብራራሉ። ለዚህም የመንግስት ስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ አወቃቀር እነርሱ በሚፈልጉት ቅኝት እንዲመራ ፖሊሲ ቀርጸው እንደሚሰጡ ይተነትናሉ። አቶ መሀመድ አሸባሪው ህወሓት ለእነዚህ ሃይሎች መሳሪያ በመሆን እያገለገለ እንደሆነ ከጅማሮ አንስቶ ያለውን ሁኔታ በዝርዝር አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን የሚያስረዱት አቶ መሀመድ በ1970ዎቹ የነበረው ትግል እነዚህን ልዩነቶች አቻችሎ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ዓላማ ያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን አጀንዳ ያነገቡ በርካታ ሃይሎች እንደነበሩ የሚገልጹት አቶ መሀመድ ህወሓት ግን በረሃ በነበረበት ወቅት በቀረጸው ማንፌስቶ የትግራይ ሪፐብሊክ ለመመስረትና ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ወስኖ እንደነበር አብራርተዋል። በወቅቱ ብዙዎች ይህንን ሀሳብ እንደተቃወሙትና በኋላም ፕሮግራሙን ደብቀውት ለአንድ ዓመት ያህል ያለፕሮግራም መቆየታቸውን አያይዘው ገልጸዋል።

ህወሓት የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው ይህን ፕሮግራም ሳያስተካክል እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ መሀመድ በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት በተቋቋመበት ወቅት ሁሉንም ታጣቂ ሃይሎች ያሳተፈ ውይይት እንዲደረግና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምእራፍ የሚያሸጋግር ስርዓት እንዲፈጠር ታስቦ የነበረ ቢሆንም ህወሓት የራሱን መንገድ መከተሉን ይገልጻሉ። በዚህ ምክንያት አንዳንዶቹ መድረኩን ጥለው መውጣታቸውን የሚያስታውሱት አቶ መሀመድ ይህን ተከትሎ ህወሓት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲውን ለማሳካት በሚያመች መንገድ ህገ መንግስት ማርቀቁንና ምርጫዎችን ማካሄዱን አብራርተዋል።

ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የመንግስትን የአስተዳደር እርከኖች እንዲሁም ኢኮኖሚውን በበላይነት በመቆጣጠር አንዱን ቡድን ከሌላው ቡድን ጋር እንዳይስማማና እርስ በርስ በጠላትነት እንዲተያይ ሲሰራ መቆየቱን አቶ መሀመድ ገልጸዋል። በዚህ የስልጣን ቆይታው ህወሓት የፈጸማቸውን ድርጊቶች በማስታወስ ቡድኑ እታገላለሁ የሚለው ለትግራይ ህዝብ ሳይሆን ለራሱ ስልጣን ማራዘሚያ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ህወሓት በተከተለው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ከኤርትራ ጋር ጦርነት መክፈቱን የሚያብራሩት አቶ መሀመድ በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱን ፖለቲካ በሚገባ ለተገነዘበው ሰው ቡድኑ በውጭ ሃይሎች የሚነዳ መሆኑን ይረዳል ይላሉ። ይህ ቡድን ከውጭ በሚሰጠው ድጋፍ እንደሚተነፍስ የሚገልጹት አቶ መሀመድ ለእነዚህ ሀይሎች መጠቀሚያ መሳሪያ በመሆን ቀጠናውንም ጭምር እንደሚያውክ አስረድተዋል። አሸባሪው የህወሓት ቡድን የትግራይን ህዝብ በምንም መልኩ አይወክልም በማለት የሚገጹት አቶ መሀመድ በስልጣን ቆይታው ተቃዋሚዎችን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ እንዲከስሙ አሊያም እንዲዳከሙ ማድረጉንም አስረድተዋል።

 ምእራባውያን ቀጠናውን ለመቆጣጠር እንዲያስችላቸው ላለፉት 16 ዓመታት የከፋፍለህ ግዛ ፖለሲ መቅረጻቸውን ይህንንም በህወሓት በኩል ሲያስፈጽሙ መቆየታቸውን አቶ መሀመድ ያስረዳሉ። በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር የሽግግር መንግስት ተመስርቶ አዲስ የመንግስት አስተዳደር እንደሚዘረጋ ተስፋ የተደረገበት እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ መሀመድ እርሳቸውም በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸውና ለአራት ዓመታት ያህል ዲፕሎማት ሆነው ማገልገላቸውን ይገልጻሉ። ከዚህ በኋላ ግን የነበረው የፖለቲካ አካሄድ ትክክል አለመሆኑን በመገንዘባቸው ስራቸውን በመልቀቅ ትግል መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ምእራባውያን ህዝቡን በመከፋፈል በቀጠናውም ሆነ በኢትዮጰያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ልዩነቶች እንዲሰፉ ማድረጋቸውን የሚያስታውሱት አቶ መሀመድ አሁን ግን የህዝቡ ንቃተ ህሊና እያደገ በመምጣቱ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ አንድነት የሚጠናከርበት ሁኔታ መጀመሩን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም