ቀጥታ፡

የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪዎች ግጭት የመፍጠር ሴራ በኅብረተሰቡ ትብብር እየከሸፈ ነው

አዲስ አበባ ነሃሴ 15/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪዎች ሐሰተኛ መረጃ በመንዛት ግጭት የመፍጠር ሙከራ በኅብረተሰቡ ትብብር እየከሸፈ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሠላም፣ የዜጎች አንድነትና ትብብር ምቾት የማይሰጣቸው አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ዛሬም አገር ለመበተን ግንባር መፍጠራቸውን በአደባባይ አውጀዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስደፈርና የዜጎችን አንድነት ለመሸርሸር ጥምረት የፈጠሩት ሁለቱ የሕዝብ ጠላቶች እርስ በእርስ እንኳን እንደማይተማመኑ የኋላ ታሪካቸውና አመሰራረታቸው ምስክር ነው።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎችና ሸኔ ሽብርና ግጭት በመፍጠር አገር ለማተራመስ በአደባባይ ተጣምረው እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ "ሸኔ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወያኔ ነው" የሚለውን ቡድን ለመመከት የአማራ፣ አፋርና ኦሮሚያ ክልሎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሕልውና ዘመቻውን ተከትሎ በሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳዳር ዞኖች የሀይል መሳሳት ያለ የመሰላቸው ቡድኖቹ በሀሰት ፕሮፖጋንዳና በተግባር በሚገለጽ ትንኮሳ ሕዝብ ለማሸበር እየሞከሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በአጣዬ አካባቢ "ዛሬም እንደትናንቱ ግጭት ሊነሳ ነው" በሚል የፈጠራ ወሬ ሕዝቡ ቀዬውን ለቆ እንዲወጣ የማድረግ ሙከራ መኖሩን ጠቁመዋል።

ከአፋርና ከኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች በጋራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው በሐሰተኛ ወሬ የሚረበሽም ሆነ ግጭት ውስጥ የሚገባ ሕዝብ አይኖርም ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደር ከኅብረተሰቡና ከአጎራባች ዞኖች ጋር በመተባበር ከ200 በላይ የግጭት ነጋዴ ሰርጎ ገቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡም ያልተፈጠረውን ተፈጠረ እያሉ የሐሰት መረጃ ከሚያራግቡ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

ዋና አስተዳዳሪው የአሸባሪዎቹን ቡድኖች ተልዕኮ ለማስፈጸም ውዥንብር በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም