ቀጥታ፡

የዲስትሪክቱ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት 56 ሚሊዮን ብርና ደም ለገሱ


ጭሮ፣ነሐሴ15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጭሮ ዲስትሪክት ሰራተኞች የሀገርና የህዝብ ሰላም ዘብ ጠባቂ ለሆነው መከላከያ ሰራዊት ደጀንነታቸውን ለማሳየት ከወር ደመወዛቸው 56 ሚሊዮን ብር እና ደም ለገሱ።


የተቋሙ ሰራተኞች በሀገር አንድነት ጉዳዮች ውይይት በማካሄድ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ላይ የጋራ ስምምነት በመፍጠር፤ የወር ደመወዛቸውንና ደም ለግሰዋል።


እንዲሁም ለሶስተኛው አረንጓዴ አሻራ አዲስ የእጽዋት ማዕከል በማዘጋጀት ልማትን የማስቀጠል ከፍተኛ ንቅናቄ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡


የዲስትሪክቱ የፋይናንስ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ስዩም መና እንዳሉት ሰራተኞቹ የጥፋት ድርጊቱን በሀገሪቷ ሀብትና ንፁሃን ህዝቦች ሕይወት ላይ እየፈፀመ የሚገኘውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ የሚደረገውን ዘመቻ በመደገፍ ከወር ደመወዛቸው 56 ሚሊዮን ብር እና ደም ለግሰዋል።


የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ለሶስተኛው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 5 ሺህ ለማህበረሰቡ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ሀገር በቀል ችግኞችን በመትከል ከመከላከያ ሰራዊቱና ከመንግስት ጎን መቆማቸውንም አቶ ስዩም ገልፀዋል፡፡


ስራ አስኪያጁ አክለውም የተቋሙ ሰራተኞች አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊቱና በንፁሃን ወገኖች ላይ የሚፈፅመውን የግፍ ጭፍጨፋ በመቃወም ለሀገር ማዳን ጥሪው ምላሽ ለመስጠት ጦር ግንባር ድረስ ሄደው እስከ መዋጋት ድረስ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡


የተቋሙ አውቶሜሽን ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ አቶ አረጋኸኝ ካሳ በበኩላቸው የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ የሚመጡ የመንግስት ጥሪዎችን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


አያይዘውም የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።


አጠቃላይ የስርጭት ግንባታና የጥገና አገልግሎት ክፍል ኃላፊ አቶ ጌታሁን አበጋዝ ለሀገራችን ሰላም በጦር ግንባር ደሙን እያፈሰሰ ህይወቱን እየሰዋ ላለው የመከላከያ ሰራዊታችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙና ወደፊትም ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡


"ሀገራችንን ከአጥፊዎች የማዳን ድጋፋችን ተጀመረ እንጂ አላበቃም፣ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን እስከሚወገድ ድረስ ከመንግስታችንና ከሰራዊታችን ጎን በቁርጠኝነት እንቆማለን" ብለዋል፡፡


አሸባሪው ህወሃት በመንግስት በተናጥል የተወሰነውን የተኩስ አቁም ወደ ጎን በመተው በአጎራባች አፋርና አማራ ክልሎች ላይ እየፈጸመ ያለውን የጭካኔ ድርጊት የተለያዩ ዓለም አቀፍና የሃገር ውስጥ ተቋማት እያወገዙት ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም