ብሔራዊ የደም ባንክ ዘመናዊ የደም መመርመሪያ መሳሪያዎችን ወደ ሥራ አስገባ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የደም ባንክ ዘመናዊ የደም መመርመሪያ መሳሪያዎችን ወደ ሥራ አስገባ
ነሐሴ14/2013(ኢዜአ) ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት አምስት ዘመናዊ የደም መመርመሪያ መሳሪያዎችን ወደ ሥራ አስገባ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ዛሬ በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
የመመርመሪያ ማሳሪያዎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ አዳማ፣ባህርዳር፣ጅጅጋና ሐዋሳ ከተሞች የተከሉ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ 24 የደም ባንኮች የሚመጡ የደም ናሙናዎችን ይመረምራሉ።
ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ የደም ህክምና ለመስጠት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በደም ባንኮች መካከል ጥራቱን የጠበቀና የተሳለጠ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ በበኩላቸው የደም መመረመሪያ መሳሪያዎቹ በ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተገዙ ገልጸው፤ ክፍያውን በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከአቅራቢ ድርጅቱ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ 'ኤች አይ ቪ'፣ 'ሄፓታይተስ ቢ' እንዲሁም የደም አይነት ምርመራዎችን እንደሚያከናውኑም ጠቁመዋል።
መሳሪያዎቹ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እስከ 900 ሺህ ደም ናሙናዎችን ለመመርመር እንደሚያስችሉም ነው ያነሱት።
የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በሰዓት እስከ 200 ናሙናዎችን የመመርመር አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህም በሰው ኃይል ሲከናወን የነበረውን የደም ናሙና ምርመራ ሂደት እጅጉን ያሻሽለዋል ብለዋል።
አንድ ባለሙያ በአንድ ቀን ውስጥ የሚያከናውነው የምርመራ አቅም ከ180 ናሙናዎች እንደማይበልጥ በአስረጂነት አንስተዋል።