በምእራባውያን ወጥመድ ሥር ከወደቁ ሀገራት ሊወሰድ የሚገባ ልምድ - ኢዜአ አማርኛ
በምእራባውያን ወጥመድ ሥር ከወደቁ ሀገራት ሊወሰድ የሚገባ ልምድ
በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)
በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኘው ኢራቅ በተለያዩ ዓመታት ጦርነቶችን ያስተናገደች ሀገር መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን እ.አ.አ በ1990 የተቀሰቀሰው ጦርነት ምዕራባዊያንን ያሳተፈ እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይገልጻሉ። አሜሪካ አጋሮቿን አስተባብራ ጦሯን ወደ ኢራቅ በማዝመት በፈጸመችው ወረራ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እና የባሕል ውድቀት እንደደረሰባት መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢራቅ የተካሄደው ጦርነት በሀገሪቱ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ቁርሾ ፈጥሮ ያለፈ ሆኗል።
ይህ ጦርነት ከኢራቅ አልፎ ለተቀረው አረብ አገራትም በመትረፍ እ.አ.አ በ2014 ለተቀሰቀሰው የአረብ ነውጥ /የአረብ ስፕሪንግ/ እየተባለ ለሚጠራው ህዝባዊ አመጽ መነሳሳት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። አሜሪካ በኢራቅ ላይ በፈጸመችው ወረራ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሳዳም ሁሴን ከስልጣን ከተወገዱ ጊዜ ወዲህ ኢራቅ ውስጥ እስካሁን ያልተፈቱ መጠነ ሰፊ ችግሮች መኖራቸውን ምሁራን ይገልጻሉ።
በኢራቅ ውስጥ የተፈጠረው ጦርነት ሀገሪቱን ለከፍተኛ ድህነት የዳረጋት ከመሆኑም ባሻገር ከተቀረው ዓለም ተለይታ እንድትቀር አድርጓታል። በሀገሪቱ ውስጥ ጥላቻ እንዲባባስ በማድረግ ሕዝቦች እርስ በእርስ ተቻችለው ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት እና የቆየ ታሪክ እንዲሸረሸር አድርጓል። በዚህ ምክንያት ኢራቅ ራሷን የማስተዳደር አቅሟ በመዳከሙ በባዕዳን አገሮች እየተመራች ሕዝቦቿም በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጓታል።
በውጭ ተዋናዮች የሚዘወረው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ አስር ዓመታት ያለፈው ሲሆን ወደ 400 ሺህ የሚጠጋ የሰው ህይወት መጥፋቱን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ጦርነቱ እየሰፋ በመጣ ቁጥር የውጭ ሀይሎች በገንዘብ፣ በጦር መሣሪያዎች እና ተዋጊዎችን በመላክ የሚፈልጉትን ቡድን በመደገፍ ችግሩ እንዲቃለል ማድረግ ሲገባቸው እንዲባባስ አድርገዋል። ጦርነቱ እ.አ.አ በ2011 የሀገሪቱ ዜጎች ባነሱት የዲሞክራሲ ጥያቄ እንዲሁም ሙስናን በመቃወም የተቀሰቀሰ ቢሆንም የውጭ ሃይሎች እጃቸውን በማስገባታቸው ምክንያት እስከዛሬ ድረስ ወደ ማያባራ እልቂት ሊያመራ ችሏል።
የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በውጭ ተዋናዮች ድጋፍ በተቀጣጠለው ጦርነት ምክንያት ከሶሪያ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለስደት ተዳርገዋል፤ ከ6.7 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ተፈናቃይ ሆነው ካምፕ ውስጥ ተጠልለዋል። ከአስር ዓመቱ ጦርነት በኋላ በመላ ሀገሪቱ ያሉ መሠረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። በጥቅሉ በምእራባውያን የተለኮሰው እሳት ተቀጣጥሎ ሶሪያ የፈረሰች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል።
ሊቢያውያን በሙሀመድ ጋዳፊ የአስተዳደር ዘመን ምንም እንኳን በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ ችግር እንደነበረባቸው ቢነገርም የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ነበሩ። ሊቢያ በነዳጅ ሀብት የምትታወቅ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ዜጎቿ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በነፃ ያገኙ እንደነበር ይታወቃል። ምእራባውያን ተቀናጅተው በሊቢያ ላይ ጣልቃ በመግባት የጦር ሀይላቸውን በማዝመት ጋዳፊን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ የሀገሪቱ ዜጎች ሰላም ናፍቋቸዋል። በአሁኑ ወቅት በሊቢያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ተዋናዮች በዝተዋል፤ ሀገሪቱ ግን እየፈረሰች ትገኛለች።
አሜሪካ አፍጋኒስታን የገባችው የአሜሪካንን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ አሸባሪዎችን ለማጥፋት እንጂ አፍጋኒስታንን ለመገንባት አይደለም በማለት በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን መናገራቸው ይታወሳል። አሜሪካ እኤአ በ2001 አፍጋኒስታንን ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ ከ3ሺሀ 950 በላይ የጥምር ኃይሉ አባላትን ጨምሮ ከ64 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ 20ሺህ 660 የአሜሪካ ወታደሮች ደግሞ አካለ መጉደሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። አሜሪካ በአፍጋኒስታን በቆየችባቸው 20 ዓመታት ከ2.4 ትሪሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንደምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ትንተና ከሆነ አሜሪካ ይህን ገንዘብ ከጦርነት ይልቅ ለልማት አውላው ቢሆን ኖሮ አስካሁን ከ5.2 ትሪሊየን ዶላር በላይ ይደርስላት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ዓላማዋን ማሳካት ተስኗት ጦሯን ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን ስታስወጣ አፍጋናውያን መግቢያ መውጫ ጠፍቶባቸዋል። የታሊባን አማጽያን ባልታሰበ ፍጥነት ሀገሪቱን ሲቆጣጠሩ የተፈጠረው ቀውስ እጅግ አሳዛኝ ነበር። የጀርመን መራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክል “ኔቶ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠመው ትልቁ ውድቀት ነው” ብለውታል። ይህን የቻንስለሯን መልዕክት የዘርፉ ምሁራን በገደምዳሜው የአሜሪካ ውድቀት የታየበት ውሳኔ ለማለት የተፈለገበት እንደሆነም ይገልጹታል፡፡
የጀርመን የክርሲቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት CDU ፓርቲ ሊቀመንበር አርሚን ላሼት በበኩላቸው በአፍጋኒስታን የነበረው ተልዕኮ «የተሳካ አልነበረም» ካሉ በኋላ «ኔቶ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የገጠመው ታላቁ ውድቀት ነው» በማለት ተናግረዋል።
ምእራባውያን እጃቸውን የሚያስገቡባቸው ሀገራት የመጨረሻ ውጤቱ የእርስ በርስ ግጭት፣ ድህነትና ስደት ብሎም ያልተረጋጋና በሞግዚት የሚመራ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት መፈጠር ነው። ኢራቅ፣ ሶሪያና ሊቢያ ለአብነት ተገለጹ እንጂ በርካታ ሀገራት በተመሳሳይ ፈተናዎች ውስጥ አልፈዋል። የምእራባውያንን ተጽእኖ መቋቋም የቻሉ ሀገራት ዜጎቻቸውን ወደ ተሻለ ህይወት ማሸጋገር የቻሉ ሲሆን ሸብረክ ያሉቱ ደግሞ የፈረሱ እና ውስብስብ ችግሮች ያለባቸውን ሀገራት ለመምራት ተገደዋል።
የዓለም የታሪክ አውድ እንደሚያመላክተው እንደ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ቱርክ፣ ባህሬን፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ኮርያና ቬየትናም የመሳሰሉ ሀገራት በአንድ ወቅት ከአሜሪካን እና ከአንዳንድ አውሮፓ ሀገራት የተሰነዘረባቸውን ጣልቃ ገብነት እና ጫና በጋራ በመቆም ፊት ለፊት ተጋፍጠው ራሳቸውን አስከብረዋል። በዚህም አሁን ላይ በኢኮኖሚ አቅማቸውና በዘመናዊ የፖለቲካ አስተዳደራቸው፣ በቴክኖሎጂ ምጥቀታቸውና በማኅበራዊ ዕሴታቸው እጅግ ዘመናዊ ከሚባሉት ሀገራት መካከል የሚመደቡ መሆን ችለዋል።
በአንጻሩ ደግሞ በአንድነት መቆም እና የሚሰነዘርባቸውን ጣልቃ ገብነት መመከት ያልቻሉ እንደ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን (ለሁለት እንድትከፈል ማድረጋቸው)፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ የመን የመሳሰሉት ደግሞ ዕጣ ፈንታቸው አሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እንደሚፈልጉት ሆነው መገኘታቸውን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ምእራባውያን የኢትዮጵያ ካለችበት የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂክ የቦታ አቀማመጥ እና አቅም ብታጎለብት በቀጣናው ላይ ልትፈጥር የምትችለውን ተጽእኖ በስጋት በመመልከት በቀጣናው አለን የሚሉትን ጥቅም ለማግኘት ፈተና ትሆንብናለች በሚል ስጋት በቅርበት እንደሚከታተሏት ይታወቃል። በተለያዩ ጊዜያት ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመመስረት የተደረጉ ጥረቶችን ለማደናቀፍ ልዩ ልዩ ስልቶችን ተጠቅመዋል።
ታደሰ በቀለ “ከቀዳማዊ እስከ ቀዳማዊ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ለማዳከም በነበራቸው ፍላጎት “የትግሬ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት እና የኦሮሞ መንግሥት” በሚል ከፋፍለው እንደነበር ያስረዳሉ። በተመሳሳይ ጣሊያን “የኤርትራ መንግሥት፣ የአዲስ አበባ መንግሥት፣ የኦሮሞ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት፣ የሲዳማ እና የሱማሌ መንግሥት እና የሀረር መንግሥት” በሚል ወደ ተበጣጠሰ ሀገርነት እንድትቀየር ሲሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያ አንድነቷን አጠናክራ ሀገረ-መንግስት ለመመስረት እንቅስቃሴ በመጀመሯ ምክንያት የተለመደ የማዳከም ስትራቴጂያቸውን ኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር እየሰሩ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የጀመረው ለውጥ ከኢትዮጵያ አልፎ ምሥራቅ አፍሪካን ለማልማት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በውጭ ኃይሎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን መፍጠሩ ብዙዎች የሚግባቡበት ሀሳብ ነው።
በዚህ ምክንያት ምእራባውያን የሽብርተኛው ህወሓት ጠበቃ በመሆን መንግስትን ለማሸማቀቅ በሁሉም አቅጣጫ ዘመቻ ከፍተው እየሰሩ ይገኛሉ። ያለው አማራጭ የተከፈተውን ዘመቻ ተቋቁሞ መሻገር አሊያም ደግሞ እንደ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያና የመሳሰሉት ሀገራት በሞግዚት አስተዳደር መኖር ነው።
የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ ድርድር አለማወቃቸውን ሲሆን አሁን እያሳዩ ያሉትም ይህንኑ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ይስማሙበታል፡፡