ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱርክ ጉብኝት የኢንቨስትመንት ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14 / 2013 (ኢዜአ)የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የቱርክ ጉብኝት የኢንቨስትመንት ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከቀናት በፊት በቱርክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤  የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሁለቱ ሀገሮች በወታደራዊና በውሃ ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሀገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን የቆየ ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከርም ተስማምተዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቱርክ ባለሃብቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ምዕዋለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ።

ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዳላትም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር እውነቱ በሃይሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ቱርክ  ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዕድገት ጉልህ አበርክቶ አላት።

በአሁኑ ወቅት  ከ240 በላይ የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው፤ ይህም ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት እድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።

የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቱርክ ጉብኝትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ ያጠናክረዋል ነው ያሉት።

እንደ ዶክተር እውነቱ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ከተሰማሩ 245 የቱርክ ባለሃብቶች መካከል 150 የሚሆኑት በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ናቸው።

ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ባለሃብቶቹ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ አማራጫቸውን እንዲያሰፉ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።

የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጰያ ምዕዋለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ከሚገኙባቸው ዘርፎች ውስጥ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣መሰረተ ልማት፣ ትራንስፖርት ፣ግብርና ትምህርትና ሪልስቴት ይገኙበታል።

በዚህም ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ከ30ሺ በላይ ደግሞ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም