ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ላይ ሊፈፀም የሚችልን የምጣኔ ሃብት አሻጥር ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14 / 2ዐ13 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ ላይ ሊፈፀም የሚችልን የምጣኔ ሃብት አሻጥር ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አሸባሪው የህውሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በጦርነት ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሃብት ሴራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አመለካች ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የልማት ኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ተስፋዬ ጮፈና ለኢዜአ እንደገለጹት በጦርነት ውስጥ የተለያዩ የምጣኔ ሃብት አሻጥሮች ሊፈፀሙ ይችላሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የመንግስትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም ለማዳከም የሚደረግ አሻጥር ይኖራል ነው ያሉት።

በምጣኔ ሃብት ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ጠላትን ለማገዝ በሚፈጥሩት የምጣኔ ሃብት አሻጥር ሊገለጥ እንደሚችል በማንሳት በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም ይህ መሆኑን አብራርተዋል።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን አገርን ለማፍረስ ከያዘው አጀንዳ ጎን ለጎን በምጣኔ ሃብት ውስጥ የአሻጥር ሰንሰለት በመዘርጋት ዜጎች ከፍተኛ ችግር ላይ እንዲወድቁ ከማድረግ አይቦዝንም ብለዋል ዶክተር ተስፋዬ ።

በማብራሪያቸውም ምርት ማሸሽና ገበያው እንዳይረጋጋ ማድረግ፤ የመንግስትን የምጣኔ ሃብት መዋቅር ለማዳከም የሚደረጉ ተግባራትና የውጭ ምንዛሬ በህገ ወጥ መንገድ መመንዘር መገለጫዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን መሰረተ ልማቶችን በማውደም በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ከመፍጠር ባለፈ ከግብረ አበሮቹ ጋር የመንግስትን መዋቅር ለማዳከም የሚሰራቸውን ተግባራትም አንስተዋል።

መንግስት ለዜጎች የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በአግባቡ እንዳያደርስና ህዝብ እንዲማረር ለማድረግ የመረጃ መረቦች ላይ ጥቃት መፈጸም ሌላኛው አሻጥር መሆኑን አንስተዋል።

ችግሮቹን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ደረጄ ደጀኔ በበኩላቸው የህወሃት አሸባሪ ቡድን በምጣኔ ሃብት ውስጥ አሻጥር በመፍጠር በፖለቲካ የበላይነት ለመያዝ ብዙ ይጥራል ነው ያሉት።

ለተግባራቸው ማስፈጸሚያ በውጭና በአገር ውሰጥ በምጣኔ ሃብት የተሳሰሯቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች በመኖራቸው እነሱን በመለየት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አንደኛው መፍትሄ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው ሚክስድ ኢኮኖሚ በመሆኑ እያከናወናቸው ያሉትን የገበያ የማረጋት ተግባራት ማጠናከር ሌላኛው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምጣኔ ሃብት አሻጥር የሚፈጥረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ለመፍታት ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን መስራትም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም