ቀጥታ፡

የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔን የጥፋት ሴራ አንድ ሆነን እናመክናለን!

አምቦ፤ ነሐሴ 14 / 2ዐ13 (ኢዜአ) የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጥምረት ኢትዮዽያን ለማፍረስ ያለመ በመሆኑ ይህንን የጥፋት ሴራቸውን አንድ ሆነን እናመክናለን ሲሉ የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ።

ነዋሪዎቹ የአሸባሪዎቹን ጥምረት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ በአምቦ ከተማ አካሄደዋል።

በሰልፊ ላይ ነዋሪዎቺ "ህወሃትና ሸኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ናቸው፣ ሸኔ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወያኔ ነው፣ በመስዋዕትነት ያገኘነውን ነፃነት በመስዋዕትነት እንጠብቃለን፣  ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ዘብ እንቆማለን" መልዕክቶችን አስተጋብተዋል።

የወያኔና የሸኔን ጋብቻ በጽኑ እንቃወማለን፣ ባንዳና የውጭ ጠላቶችን እንመክታለን ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡

በሰልፉ ከታደሙት ውስጥ ወጣት እጅጉ መኮንን በሰጠው አስተያየት፤ ህወሓት በኢሬቻ በአል በኦሮሞ ወጣቶች ላይ ታሪክ የማይዘነጋው የጭካኔ ተግባር መፈፀሙንም አስታውሷል።

የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ጥምረት ኢትዮዽያን ለማፍረስ ያለመ ሴራ በመሆኑ ሴራቸውን አንድ ሆነን እናመክናለን፣በዕርዳታ ሰበብ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ የውጭ ሀገራትንም እናወግዛለን ብሏል።

ወይዘሮ መስከረም ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ህወሓት የጭካኔ ተግባሩን በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲፈፀም ምንም ያላለው ሸኔ ዛሬ ህወሓትን ለመደገፍ ጥምረት ፈጥሬያለሁ ማለቱ አረመኔነቱንና ከሃዲነቱን ይፋ ማድረጉን ያመላክታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት የሆኑትን ህወሓትንና ሸኔን ለማስወገድ የሚካሄደውን ትግል በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

ሸኔ የኦሮሞ ተወላጆችን ሲያስጨርስ የነበረ የህወሓት ቅጥረኛ ተላላኪ በመሆኑ አምርረን እንቃወማለን ያሉት ደግሞ አቶ እጅጉ ናፒር ናቸው፡፡

የኦሮሞ ህዝብም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ሁለቱን ቡድኖች ለማስወገድ መታገል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳህሉ ዲርብሳ ፤ ሸኔ ቀደም ሲል በወያኔ ዘመን የደረሰበትን ግፍ እና መከራ ወደ ጎን ትቶ ከቡድኑ ጋር ጥምረት መፍጠሩ ሀገር የማፍረስ ዓላማ አንድ ስላደረጋቸው ነው ያሉት፡፡

ይሁንና ኢትዮጵያ በጠላት ሴራ እንደማትፈርስ ገልጸዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲሪሪሳ ዋቁማ በበኩላቸው ፤ አሸባሪ ቡድኖቹ ተጣምረው ሀገርን 

ለማፍረስ የሸረቡት ሴራ ለማምከን ሁሉም ኢትዮዽያዊ በተባበረ ክንድ ልንታገለው ይገባል ብለዋል።

በሰልፉ ላይ ከአምቦ ከተማና ምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች የተወጣጡ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም ነዋሪዎች በፈረሰኛና ተሽከርካሪዎች ታጅበው ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም