ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ የሕልውና ፈተና መገናኛ ብዙሃኑ በቅጡ ተረድተው እየሰሩ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ የሕልውና ፈተና መገናኛ ብዙሃኑ በቅጡ ተረድተው እየሰሩ አይደለም
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 14 /2013 ዓ.ም (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ የሕልውና ፈተና መገናኛ ብዙሃኑ በቅጡ ተረድተው እየሰሩ አይደለም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የሚዲያ የስራ ሃላፊዎች ገለጹ።
በአሁኑ ጊዜ የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ጉዳይ የሚዲያዎች ቅድሚያ የትኩረት አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል።
የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ እንደሚለው ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ የነበረው ህወሃት መራሹ ስርዓት ሚዲያን ማበልጸግና ማሳደግ አልቻለም።
የግል ወይም የንግድ መገናኛ ብዙሃን የሚባሉት በዘውግ እንዲታጠሩ ሲደረጉ መቆየታቸውንም አንስቷል።
መገናኛ ብዙሃኑ በኢትጵያዊነት፣ አገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች፣ ታሪካ ላይ ዜና ነክ ስራዎችን እንዳይይሰሩና ፈቃድ እንዳያገኙ መደረጋቸውን አስታውሷል።
ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ስትገባ በነበረው የአሰራር ማነቆ ተቀይደው ዝምታን የመረጡ እንዳሉ ገልፆ የሚዲያ አመራሮችና አርታኢያን ከዚህ ሊወጡ ይገባል ብሏል።
"ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ናት፣ የክተት አዋጅ ታውጇል" የሚለው ጋዜጠኛ ጥበቡ፤ መገናኛ ብዙሃን ከብዙ የፌስታና ጨዋታ ስራዎች ወጥተው የአገር ህልውና ላይ ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸው ብሏል።
የሸገር ሬዲዮ የስራ አስኪያጅ ረዳትና የፕሮግራም አዘጋጅ ግርማ ፍስሐ፤ መገናኛ ብዙሃን ለአገር ማበርከት ካለባቸው ሚና አንጻር አሁን ላይ ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ማለት አይቻልም ብሏል።
የዚህ ዋነኛ መክንያትም የተጠናከረ መረጃ የማግኘት ችግርና በብሄራዊ ጥቅም ላይ ያለው አረዳድ ችግር መሆኑን ያነሳል።
በየትኛውም አገር ሚዲያ በአገር ጥቅም ጉዳይ አይደራደርም ያለው ግርማ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም በአገር ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም ሊይዙ ይግባል ብሏል።
'ከምንምና ከማንም በላይ አገር ትበልጣለች' የሚለው ጋዜጠኛ ግርማ ፍስሃ በአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የሚደራደር የሚዲያ ተቋምም የሁን ባለሙያ መኖር የለበትም ነው ያለው።
የቴቪ ናይን ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል አባተ መገናኛ ብዙሃን ገለልተኛ የሚሆኑበት ሁኔታዎች እንዳሉ ይናገራል።
ኢትዮጵያን አሁን በገጠማች የህልውና ፈተና ግን ሚዲያው ገለልተኛ የሚሆንበት አጋጣሚ የለም ነው የሚለው።
በመሆኑም ሁሉም የሚዲያ ተቋማት ከመንግስት ጎን ቆመው እንዲሰሩ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ትልቁን ሚና መወጣት አለባቸው ብሏል።
በርካታ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ አድሎ በመፈፀም የተጠናከረ ዘመቻ በመጀመራቸው ይህን ጫና የመክትና ከአገር ጥቅም ጎን መቆም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነት መሆን አለበት ነው ያለው።
ከሶሻልሚዲያ በተሻለ ዋናው ሚዲያ ቢሰራ አገራዊ ብዥታን መቀየርና የውጭ ሚዲያ ዘመቻውን መመከት ያስችላል ብሏል።
በተለይም በማህበራዊ ሚደያ የሚሰጩ መረጃዎች በህዝብ ዘንድ ብዥታ እንዳይፈጥሩ ከመመከት በተጨማሪ መንግስት የኮሚኬሽን ስትራቴጂ ሊያበጅ ይገባል ብለዋል ጋዜጠኞቹ።
ጋዜጠኞችም ወቅታዊ መረጃ የሚያኙበትንና በግንባርም ተገኝተው የሚዘግቡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል የሚዲያ ሃላፊዎቹ።
ለጋዜጠኞች የጦርነት አዘጋገብ ስልጠናዎችን በመስጠት የአገር ህልውና ዋነኛ አጀንዳዎቻቸው አድርገው እንዲሰሩ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የህወሃት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል እገባለሁ ብሎ ጦርነት በማወጅ በአሁኑ ጊዜ በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በዜጎች ላይ ወንጀል በመፈፀም ላይ መሆኑ ይታወቃል።