የሸኔንና የሕወሓትን ሀገርን የማፍረስ ስምምነት እናወግዛለን- የመቱ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሸኔንና የሕወሓትን ሀገርን የማፍረስ ስምምነት እናወግዛለን- የመቱ ከተማ ነዋሪዎች
መቱ ነሐሴ 14/2013 (ኢዜአ) የሸኔንና የሕወሓትን ሀገርን የማፍረስ ስምምነት እናወግዛለን ሲሉ የመቱ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ግፍ ሲፈፅም ከነበረው አሸባሪ ህወሀት ቡድን ጋር የሚቆም ኦሮሞን የሚወክል ቡድን ፈፅሞ የለም፤ ሊኖርም አይችልም ሲሉ ነዋሪዎቹ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል ።
ሀገርን በማዳን ዘመቻ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌታቸው ብርሃኑ እንዳሉት ሸኔና ሕወሓት ቀድሞውኑ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ልዩነቱ አሁን ላይ በይፋ ይታወቅልን ማለታቸው ብቻ ነው።
"ኦሮሞን በኦሮሞነቱ ለግድያና ለአካል ጉዳት ሲዳርግ ከነበረው ሕወሓት ጋር ስምምነት የፈጠረው ሸኔ ከኦሮሞ ሕዝብ ጠላቶች ዋነኛው እንጂ ኦሮሞን የሚወክል አይደለም " ሲሉ ተናግረዋል።
የጥፋት ሀይሎቹን ለማጥፋት በሚደረገው በማንኛውም ጥሪ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በቅርቡ ሀገርን በጋራ ለማፍረስ የተስማሙት ሸኔና ሕወሓት ቀድሞውኑ ይህንኑ ተግባር በጋራ ሲፈፅሙ የኖሩ ናቸው" ያሉት ደግሞ ኢንጂነር ሀቢብ ቡልቻ ናቸው።
"በቡድኖቹ ስምምነት የምትፈርስ ኢትዮጵያ የለችም፣ እኔም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ወደ ኋላ አልልም" ብለዋል።
"ሀገርን የማዳን የዜግነት ድርሻችንን በማንኛውም መልኩ እንወጣለን" ሲሉም ተናግረዋል።
"የአከባቢያችንን ሰላም የሚጠብቅልንም ሆነ የሀገራችንን ሉዓላዊነት የሚያስከብርልን ሌላ አካል የለም " ያሉት ኢንጂነር ሀቢብ "ሁላችንም መቼምና በየትኛውም ቦታ የዜግነት ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን" ሲሉ" አቋማቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ዘከሪያ አብዱራህማን በበኩሉ "አካባቢዬን ከተላላኪው ሸኔ ጥቃት እጠብቃለሁ፣ መከላከያ ሰራዊቱንም ለመቀላቀል ዝግጁ ነኝ" ብሏል።
"ጥንት አባቶቻችን ሀገርን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጠብቀው ለኛ ያስረከቡት በጠነከረ አንድነታቸው ነበር"ያለው ወጣቱ "እኛም ሀገራችን ከኛ የምትጠብቀውን ዋጋ ሁሉ ከፍለን ልናሻግራት ዝግጁ ነን" ሲል አስታውቋል።