አሸባሪዎቹን ህወሃትና ሸኔን የሚያወግዙና የሚቃወሙ ሰልፎች በአሰላ፣ አምቦና ዱከም ከተሞች እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪዎቹን ህወሃትና ሸኔን የሚያወግዙና የሚቃወሙ ሰልፎች በአሰላ፣ አምቦና ዱከም ከተሞች እየተካሄደ ነው
ነሐሴ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪዎቹን ህወሃትና ሸኔን የሚያወግዙና የሚቃወሙ ሰልፎች በአሰላ፣ አምቦና ዱከም ከተሞች እየተካሄደ ነው።
በአሰላ ከተማ በሚካሄደው ሰልፍ ላይ ከአርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እንዲሁም ከአሰላ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
ሰልፈኞቹ “የሃገራችን ብልፅግና በውስጥና በውጭ ጠላቶቻችን አይደናቀፍም፣ ወያኔን ባስወገደው የተባበረ ክንዳችን ሸኔን እንነቅላለን፤ ለኢትዮጵያ እዘምታለሁ የትም መቼም በምንም፤ ሸኔና ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ናቸው’’ የሚሉ መልዕክቶች አስተጋብተዋል፡፡
በአምቦ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሰልፍ ከምዕራብ ሸዋ ዞን 22 ወረዳዎች እና የአምቦ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የሁለቱ ሽብር ቡድኖች ተግባር እና የቅርብ ጊዜ ውህደት ለኦሮሞ ህዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳዩበት እንደሆነ በመግለጽ አውግዘዋል።
በተመሳሳይ በዱከም ከተማ ሰልፍ በተካሄደው አሸባሪዎቹን የማውገዝና የመቃወም ሰልፍ፤ የሰልፉ ተሳታፊዎች የአሸባሪዎቹን ትንኮሳ ለመመከት ከሀገር መከላከያ ጎን በመቆም እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
"አሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሓት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ናቸው፣ በውድ መስዋዕትነት የተጎናፀፍነውን ነፃነት በመስዋዕትነታችን እንጠብቃለን፣ ወያኔን ባስወገድነው የተባበረ ክንዳችን ሸኔን እንነቅላለን፣ ሸኔ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወያኔ ነው፣ ሸኔና ወያኔ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ቅጥረኞች ናቸው፣ የኢትዮጵያ ብልፅግና በውስጥና በውጭ ጠላቶች አይደናቀፍም" የሚሉ በሰልፉ ላይ መፈክሮች ተስተጋብዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዱከም ከተማ ከንቲባ አቶ ተሾመ ግርማ፤ ህዝቡ የሸኔን እና የወያኔን ጥምረት በመቃወም እና ሠላሙን ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኛ አቋም በማሳየቱ አመስግነዋል።
“ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገውን የአሸባሪ ቡድኖች አካሄድ ማክሸፍ የሚቻለው እንደ አሁኑ ሁሉም በጋራ ሲሰራ ነው” ብለዋል።
"ከወደቁ በኋላ ለመነሳት መፍጨርጨር ለመላላጥ" በመሆኑ ይህ የጥፋት ቡድን ከእነእኩይ ስራው በወደቀበት ተቀብሮ እንዲቀር ህዝቡ በጀመረው አግባብ የበኩሉን እንዲወጣ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።ምንጭ - ኤፍቢሲ