ቀጥታ፡

አሸባሪውን ሸኔን ከአካባቢያችን ለማሶገድ ተባብረን እንሰራለን -- ሀገር ሽማግሌዎች

ሀዋሳ፣  ነሀሴ 14/2013 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ቅጥረኛ የሸኔን አሸባሪ ቡድን ከአካባቢያችን ለማሶገድ ተባብረን እንሰራለን ሲሉ የኦሮሞ ፣ የሲዳማና የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ።

የሀገር ሽማግሌዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ሰሞኑን በሀዋሳ ተወያይተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ሁሴን ዋቆ እንደገለጹት ኦነግ ሸኔ  ከመነሻው ጀምሮ የሰው ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ንብረት ሲያወድም የነበረ ሀገርን ለማፍረስ የተቋቋመ ቅጥረኛ ኃይል ነው።

"ኦነግ ሸኔ በኦሮሞ ስም ይቋቋም እንጂ የኦሮሞን ደም ሲያፈስ የቆየ የእናት ጡት ነካሽ ነው "ብለዋል።

"ኦነግ ሸኔም ሆነ የጥፋት ተልዕኮ ሰጪው ህወሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስኪወገዱ ድረስ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተባብረን እንሰራለን"  ሲሉ አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ጉጂ ዞን ሀገር ሽማግሌ የሆኑት ግምቡ ሶርሳ በበኩላቸው "ኦነግ ሸኔ ከአጎራባች ወንድም ህዝቦች ጋር በሠላም እንዳንኖር ሲያደርግ የቆየ ዘራፊና ገዳይ ነው" ብለዋል።

አሸባሪው ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ሥነ-ልቦና የሌለው ነውረኛ ቡድን እንደሆነ ገልፀው "መንግስት በቡድኑ ላይ የሚወስደውን እርምጃ በማገዝ ሁላችንም ከተባበርን ከአካባቢያችን እናጠፋዋለን" ብለዋል።

የወላይታ የሀገር ሽማግሌ ሰይፉ ላታ በበኩላቸው ኦነግ ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ ያልሰጠውን ውክልና በጉልበት ለማግኘት የሚንቀሳቀስ የሽብር ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ በእኩይ ተግባሩ ኦሮሚያን ብቻ ሳይሆን አጎራባች ህዝቦችንም ጭምር የሚያሸብር የሁሉም ጠላት መሆኑን ጠቁመዋል።

"ብሄር ብሄረሰቦች በመተባበር አሸባሪ ቡድኑን ከአካባቢያችን እናጠፋለን " ብለዋል።

አሁን ላይ ከኦሮሚያም ሆነ ከሲዳማ ጋር የሚዋሰኑባቸው ሥፍራዎች ሠላም የሰፈነባቸው መሆኑን ገልፀው አካባቢውን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ምንም አይነት እድል እንዳይኖራቸው ህዝቡን የማስተባበር ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሲዳማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ኑሬ ኑካ በበኩላቸው ኦነግ ሸኔ ከዚህ በፊት የሲዳማንና ኦሮሚያን ህዝብ እርስ በእርስ እያባላ ህዝቡ ተረጋግቶ ወደ ልማት ፊቱን እንዳያዞር ሲያደርግ  መቆየቱን አስታውሰዋል።

የሁለቱ ህዝቦች የሀገር ሽማግሌዎች ባደረጉት የጋራ ጥረት ከሁለት ዓመት ወዲህ አንፃራዊ ሠላም መስፈኑን ጠቁመው የጥፋት ተልዕኮ አስፈፃሚዎች ሴራቸው እየታወቀባቸው መምጣቱን አስታውቀዋል።

የአካባቢው ህዝብ አሁን ላይ የአሸባሪውን አላማ በሚገባ መረዳቱን ገልፀው "ኦነግ ሸኔ ሠላማችንን ዳግም እንዳያደፈርስ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም