በአፋር ክልል አልፎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማሰብ የማይሳካ ሕልም ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል አልፎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማሰብ የማይሳካ ሕልም ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል መሬት አልፎ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ያሰበውን ማሳካት እንደማይችል የሠመራና ሎጊያ ከተሞች ከንቲባ ተናገሩ፡፡
የሰመራና ሎጊያ ከተሞች ወጣቶች የአካባቢውን ሠላም ማናጋት የሚሹ አካላትን በተደራጀ መልኩ እየጠበቁ መሆኑንም ገልፀዋል።
የከተሞቹ ከንቲባ አሊ መሃመድ እንደገለጹት የአካባቢውን ሠላም ለመጠበቅ ከ500 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመልምለው ስልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት እየተደረገ በሚገኘው ጥረትም የአፋር ማኅበረሰብ ሴት ወንድ ሳይል ወደ ልዩ ኃይል እየተቀላቀለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በ"ዳጉ" የመረጃ መለዋወጫ ስርዓት የሚተዳደረው የአፋር ማኅበረሰብ እርስ በእርስ ስለሚናበብ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትና አሸባሪውን ለማጥፋት በመሰማራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአፋር መሬት አልፌ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ማሰብ የማይሳካ ሕልም ነው ያሉት ከንቲባው የአፋር ማኅበረሰብና በሰመራና ሎጊያም የሚገኙ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ለአካባቢው ሠላም መጠበቅ ዘብ መቆማቸውን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ማንኛውም ሠላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ መኖር ይችላል ያሉት ከንቲባው ነገር ግን 'ሰመራና ሎጊያ እየኖርኩኝ አሸባሪውን በተለያየ መልኩ እረዳለሁ የሚል አካል ካለ ምሕረት የለንም' ብለዋል።
በሌላ በኩል የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በግንባር ለተሰማራው ሠራዊትና ልዩ ኃይል ሃብት የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በተቋቋመው የወጣቶች ኮሚቴ አማካኝነት እስካሁን ከከተሞቹ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ እህል ማሰባሰብ እንደተቻለም ተናግረዋል።
ከመንግስት መስሪያ ቤቶችና ከተለያዩ አካላት ቃል የተገባ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የከተሞቹ ወጣቶች በተጨማሪም አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ከንቲባው ተናግረዋል።