ቀጥታ፡

በአገር ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎች መጠናከር አለባቸው

ነሀሴ 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍና በአገር ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ለሰራተኞቹ ስልጠና እየሰጠ ነው።

በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ኃብተማርያም በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎች እያሳደሩ ከሚገኙት አሉታዊ ሁኔታ አንጸር ዘርፉን እንዴት እንጠቀም በሚል የሚሰጡ ስልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም አገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚያሰራጩትን ሃሰተኛ መረጃ ለመከላከልና አገርን ከጥፋት ለመታደግ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃምን በሚገባ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

ስልጠናው ከተሰጣቸው ባለሙያዎች በተጨማሪ በዙሪያ የሚገኙትን ከሃሰተኛ መረጃ ለመከላከልና ከጥፋት ለመታደግ ይጠቅማል ብለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስልጠናው በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን ክፍተት በእውቀት ላይ በተመሰረተ መንገድ ለመቅረፍ ያስችላል፣ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ችግሮች ደግመው እንዳይከሰቱና ትክክለኛውን መረጃ ለማሰራጨት ይረዳል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችን እንደሚጠቀሙ መራጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም