የትምህርት ማህበረሰቡ ትውልድን በእውቀት ከመቅረፅ ባሻገር በአገር አንድነት የማይደራደር አገር ተረካቢ ማፍራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ማህበረሰቡ ትውልድን በእውቀት ከመቅረፅ ባሻገር በአገር አንድነት የማይደራደር አገር ተረካቢ ማፍራት አለበት
ነሀሴ 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) የትምህርት ማህበረሰቡ ትውልድን በእውቀት ከመቅረፅ ባሻገር በአገር አንድነት የማይደራደር አገር ተረካቢ ማፍራት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ1 ሺህ በላይ መምህራንና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ጋር የመምህራን ሚና በሃገር ግንባታ እና በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ውይይት አካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መምህራን ትውልድን እውቀት ከመመገብ ባሻገር የአሸናፊነት መንፈስ የተላበሰና በአገር አንድነት የማይደራደር ትውልድ ማፍራት አለበት፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት የማይፈልጉ ውስጥና የውጭ ሃይሎች አላማቸውን ለማሳካት የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ብድር እንዳታገኝ፣ለጋሽ ሃገሮች እንዳይለግሱ በመከልከል እንዲሁም በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩ አካላት እንዳሉ አንስተዋል፡፡
ይህንን ለመመከት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በሃገር አንድነትና በሉአላዊነት አንድ በመሆን የውጪ ጫናዎችን ለመመከት ትልቅ መሳርያ መሆኑ ገልፀዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በትምህርት ስርአቱም ሆነ በሌሎች ነገሮች ጥሏቸው ያለፈው የመለያየት አሰራርና አካሄድ መስተካከል እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
በመደረኩ ተሳታፊ የነበሩ መምህራን በበኩላቸው እንደ ጤና ባለሙያዎች ሁሉ እነሱም በአገር ማዳኑ ዘመቻ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል፡፡
ከራሱ ይልቅ የሃገር ደህንነት ቅድሚያ ሰጥቶ ወደ ግዳጅ የዘመተው የመከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደመወዝ ከመለገስ ጀምሮ እስከ መዝመት ድረስ ፍላጎት ያላቸው መምህራን እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡