ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ደሴ (ኢዜአ) ነሀሴ 13/2013 ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ቡድን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለሚገኙ ዜጎች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት አቶ ሙክታር ዳውድ ድጋፉን ዛሬ በደሴ ከተማ ተገኝተው አስረክበዋል።
አቶ ዳውድ በዚህ ወቅት እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የሚያደርሰውን ሁለተናዊ ጉዳት በጋራ መመከት ያስፈልጋል፡፡
በሽብር ቡድኑ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ከድጋፉ መካከል 600 ብርድ ልብስ፣ 150 ፍራሽ፣ 200 ጥንድ አንሶላ፣ 100 ባለ 25 ሊትር ጀሪካን ዘይት፣ ከ30 ኩንታል በላይ ሩዝ እና ማካሮኒ ይገኙበታል፡፡
ከቄያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እንደሚጋለጡ የጠቆሙት አቶ ሙክታር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓት ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ ተቋሙ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ በበኩላቸው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት የህዝብ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ዜጎች ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለሰጠው ፈጣን ምላሽ አመስግነው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
"ጊዜው የምንረዳዳበትና የምንተጋገዝበት ነው" ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፣ "በሁሉም ዘርፍ ህብረታችንን በማጠናከር የአሸባሪውን ህወሓት ቀብር ማፋጠን ይኖርብናል" ብለዋል፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ እሸቱ በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ቁጥር ከ60 ሺህ መብለጡን ተናግረዋል።
በመንግስት በኩል ማህበረሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ችግሩን ከማቃለል ባለፈ ሌሎችን እንደሚያነሳሳ ገልጸዋል።
ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ "ሁሉም በሚችለው ድጋፍ በማድረግ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በጋራ ማለፍ ይገባል" ብለዋል።
ቦንጋ፣ ጅግጅጋና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ በጉዞ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል::