ቀጥታ፡

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ከውጭ ሃይሎች ጋር በማበር የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ እየጣረ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ13/2013 (ኢዜአ) የህወሃት አሸባሪ ቡድን ከውጭ ሃይሎች ጋር በማበር የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ እየጣረ መሆኑን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ተናገሩ።
ኮርፖሬሽኑ ለአገር መከላከያ ሰራዊት የ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ጀማል፤ የኢትዮጱያን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ የልማት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም "የንዋይ እንጂ የአገር ፍቅር የሌለው" አሸባሪው ህውሃት የተገኘውን መልካም ዕድልና ልማት በማደናቀፍ ከውጭ ሃይሎች ጋር በማበር የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ እየጣረ ይገኛል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና ስጋት ከመከላከያና ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ሁሉም መመከት አለበት ብለዋል።

የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊቱ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በማንኛውም መልኩ የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘመቾች ማህበር አባላት ያሰባሰቡትን 40 ሺህ ብር ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስረክበዋል።

የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል፤ የአሸባሪው ህውሃት ቡድን ከራሱ ጥቅም ውጪ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ግድ የማይሰጠው ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያን ጠላቶች በማሰለፍ ዕኩይ ዓላማውን ለማሳካት እያደረገ ያለው ጥረት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የቀድሞ የኮሪያ ዘማች ወታደሮች በቻሉት ሁሉ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ይሰለፋሉ ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው ዜጎች ለአገር መከላከያ ሰራዊቱ እያሳዩ ያሉትን ፍቅርና እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

ህብረተሰቡ ወደ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ ስንቅ በማዘጋጀት፣ የደምና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለሰራዊቱ ያለውን ደጀንነት በተግባር አስመስክሯልም ብለዋል።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ግብዓተ መሬት እየተቃረበ በመሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጱያ ህልውና  ላይ አደጋ የጋረጠውን አሸባሪ ቡድን በመመከት እስከ መጨረሻ ለማጥፋት ዜጎች በከፍተኛ ወኔና ጀግንነት እየተረባረቡ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም