አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈታ ማስቻል የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈታ ማስቻል የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ነው
አዲስ አበባ፣ነሃሴ 13/2013 (ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈታ ማስቻል የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪል ማህበራት ድርጅት አመራሮች ገለጹ።
ሁሉም ዜጋ በሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለበትም ነው አመራሮቹ የተናገሩት።
በቅርቡ በተካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ይፈታልኛል ላሉት ፓርቲ ድምጻቸውን መስጠታቸውን ገልጸዋል ።
የህዝብ ይሁንታ ያገኘው ፓርቲ የሚዋቀረውን አዲስ መንግስት ጠንካራና የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈታ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል።
በተጨማሪ የሃይማኖት ተቋማት፣የሲቪል ማህበራትና ሌሎች አደረጃጀቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በሀገር ጉዳይ አይመለከተኝም የሚል ዜጋ መኖር እንደሌለበት ይናገራሉ።
የትኛውንም አይነት ጉዳይ ማከናወን የሚቻለው ሀገር ህልውናዋ ተጠብቆ መቀጠል ስትችል ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ለተደቀነው የህልውና አዳጋ በቂ ምላሽ እንዲሰጥ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ትክክለኛ ያለሆኑ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር አቶ መስኡድ ገበዬሁ ናቸው።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ "ስለ ሀገሬ ያገባኛል" በሚል እሳቤ እውነታውንና የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም በማሳወቅ ረገድ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን አቋም በማሳወቅ ረገድ ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም እንዲሁ።
በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ሪፖርት 'ተራ ውንጀላ' እንጂ ተአማኒነት ያለው ማስረጃ እንደማይሆንም አቶ መስኡድ ተናግረዋል።
የህወሃት መራሹ መንግስት ኢትዮጵያን ባስተዳደረባቸው 27 ዓመታት እንደ ሲቪክ ማህበራት ያሉ የህዝብን መብት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቃሱ ድርጅቶችን አፋኝ ህግ በማውጣት በሀገር ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዳይወጡ አድርጎ መቆየቱንም ነው አመራሮቹ የገለጹት።
ከዚህ አኳያ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በሀገር ግንባታ ላይ በጎ ሚና ያላቸውን አደረጃጀቶችን በመደገፍ ረገድ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበትም ተናግረዋል።