ቀጥታ፡

የሴቶች ኮከስ አባላት ለመከላከያ ሰራዊት የስንቅ ድጋፍ አደረጉ

ነሃሴ 13/2013 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት ለመከላከያ ሰራዊት የስንቅ ድጋፍ አደረጉ።
የኮከስ አባላቱ ብርድ ልብስን ጨምሮ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፎችን አድርገዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናለ፣ የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ አበባዬ ገዛህኝ ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ድጋፉን አስረክበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ከዚህ ቀደም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ከመስጠት ባሻገር የደም ልገሳ ማድረጋቸውን ምክትል አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።

የአገር መከታና የህዝብ አለኝታ የሆነውን ሰራዊት የምክር ቤቱ አባላት በማንኛውም ቦታና ጊዜ ለማገዝና ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን በመሆን ድጋፋቸውን እንደሚጠናክሩና ካስፈለገም እስከ ግንባር መለዝመት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

አሸባሪው ህወሓት ተወግዶ አገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደ ልማትና ብልጽግና እስክታዞር ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

ሴት የምክር ቤት አባላት ራሳቸው ያዘጋጁትን ስንቅ ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሰዎችን ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ድጋፍ ማድረጋቸውን የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ  አበባዬ ገዛህኝ ተናግረዋል።

ድጋፉ በአሸባሪው ቡድን እንደ አገር የተቃጣውን ጥቃት ለመመከትና አገራዊ ጥሪውን ተግባራዊ ለማድረግ በሚል ሁሉም የምክር ቤቱ ሴት አባላት የተለያዩ ስንቆችን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፤ ኢትዮጵያን ለማዳን በግንባር እየተዋደቀ ላለው ሰራዊት ለተደረገው ድጋፍ ምስገና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመመከት ለህይወቱም ይሁን ለገንዘቡ ባለመሳሳት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት አስደናቂ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላትን ደምስሰን የኢትዮጵያን ልማትና ብልፅግና እናረጋግጣለን ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ የአንድ ወር ደመወዛቸውን በማዋጣት 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሰጡ ሲሆን የደም ልገሳም አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም